የዋግ ኽምራ ሃገረ ስብከት ከ 7 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸውን የሰብዓዊ ድጋፎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረገ

6

ግንቦት 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የዋግ ኽምራ ሃገረ ስብከት ከ 7 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸውን ብርድ ልብስና ፍራሾችን ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን ያስረከቡት የሃገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ በርናባስ እንዳሉት ሃገረ ስብከቱ በሃገሪቱ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚሆን የተለያዩ የሰብዓዊ ድጋፎችን እያቀረበ ነው።

በዚህም በሃገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር እስካሁን ድረስ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸውን የሰብዓዊ ድጋፎችን ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቅረባቸውን ነው አቡነ በርናባስ ያስታወሱት።

በብሔረሰብ አስተዳደሩ የተፈናቃይ ቁጥር መጨመር ተከትሎ በተደረገው ጥሪ መሰረት በውጭና በሃገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የወገን አለኝታነታቸውን አሳይተዋል ብለዋል።

በጥሪው መሰረት 7 ሚሊየን 400 ሽህ ብር ግምት በላይ ግምት ያላቸው 3ሺህ 421 ብርድ ልብስ፣1 ሺህ 862 ፍራሽ፣800 ኩንታል ዱቄት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ መደረጉን አቡነ በርናባስ ገልጸዋል።

በውጭና በሃገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ላደርጉት ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፅህፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ቡድን መሪ ወይዘሮ ዝናሽ ወርቁ ሃገረ ስብከቱ ያደረገው ድጋፍ የተፈናቀሉ ወገኖችን ችግር የሚያቃልል ነው ብለዋል።

ሃገረ ስብከቱ በዛሬው እለት ያደረገው ድጋፍ የተፈናቀሉ ወገኖች ያሉባቸውን ችግር የለየ መሆኑን ወይዘሮ ዝናሽ ገልፀዋል።

ሃገረ ስብከቱ ላደረገው የሰብዓዊ ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

በብሔረሰብ አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት ከ89 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን በጎ ፈቃደኛ ተቋማትና ግለሰቦች ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚያደርጉትን የሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀርቧል፡፡