ሕወሓት ሰብዓዊ እርዳታን ከንጹሓን ዜጎች ቀምቶ በመውሰድ ልምድ ያለው ድርጅት ነው

ግንቦት 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሕወሓት በጦርነቱ ምክንያት የተቸገሩ ዜጎችን ለመደገፍ ወደ ትግራይ የሚላካውን ሰብዓዊ እርዳታ የመቀማት ልምዱን እያስቀጠለ መሆኑን የቀድሞ የአውሮፓ ዲፕሎማት ተናገሩ።

የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉትና በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር የነበሩት ሲሞ ፓርቪያነን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ሕወሓት ለወታዳራዊ ግጭቶች ረሓብን እንደ መሳሪያ የሚጠቀም ድርጅት ነው።

ሕወሓት በ1980ዎቹ ሲያደረግ በነበረው የትጥቅ ትግል ወቅትም ይህን ተግባር መፈጸሙን አስታውሰዋል።

አሁንም ቢሆን ሕወሓት ሴቶችን፣ ሕጻናትንና አዛውንቶችን ለመታደግ ወደ ክልሉ የሚላኩ ሰብዓዊ እርዳታዎችን እየቀማ ነው ብለዋል።

በወቅቱ በ1977 ዓ.ም በረሃብ በተጎዱ ወገኖች ስም ከተገኘ 100 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 95 በመቶውን ለትጥቅ ትግሉ እንዳዋለው አስታውሰዋል።

ዲፕሎማቱ የኢትዮጵያ መንግስት የተኩስ አቁም አውጆ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ክልሉ እንዲገባ ማድረጉ ሕወሓት የተዛባ መረጃ እንዳያሰራጭ አድርጎታልም ብለዋል።

ሕወሓት ምግብ ብቻ ሳይሆን ከ1 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች፣ ነዳጅና መድሃኒቶችን ጭምር ወስዶ ለተዋጊዎቹ መስጠቱንና ለግጭት ማስፋፊያ መጠቀሙን ተናግረዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን ሕወሓት ሁሌ ራሱንና የትግራይን ሕዝብ ተበዳይ የሚያስመስል ፕሮፓጋንዳ የሚያናፍስ ድርጅት እንደሆነም አክለዋል።

ዲፕሎማት ሲሞ መደበኛ መገናኛ ብዙሃን የሕወሓት የተሳሳቱ መረጃ የሚያጋልጡ ስራዎችንና በአፋርና አማራ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ መረጃ መስጠት እንዳለባቸውም አመላክተዋል።

አሸባሪው ህወሃት በ1977 ዓ.ም ለረሃብ የተጋለጡ ዜጎችን ለመድረስ በሚል ያገኘውን የእርዳታ ገንዘብ እህል ገዝቼበታለሁ በማለት ማጭበርበሩን የቀድሞ አባላቱ እንዳጋለጡ ከ12 ዓመታት በፊት ቢቢሲ መዘገቡ ይታወቃል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም