የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር ፍርድ ቤት ዳኞች በፍትሐብሔር ህጎች፣ በችሎትና ብይን አሰጣጥ ላይ ያለባቸውን ውስንነት ለመፍታት እየተሰራ ነው

331

አዳማ፣ ግንቦት 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች ያሉ የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር ፍርድ ቤት ዳኞች በፍትሐብሔር ህጎች፣ በችሎትና ብይን አሰጣጥ ላይ ያለባቸውን ውስንነት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር መኩሪያ ሃይሌ ገለጹ።

በተቋማትና ሠራተኞ መካከል የሚፈጠርን አለመግባባትና ቅራኔ በፍትህ ለመፍታት የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ሚና የላቀ መሆኑን አመልክተዋል።

ኮሚሽኑ የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር ፍርድ ቤቶችን በችሎትና ውሳኔ አፃፃፍ ላይ ያለውን የአቅም ክፍተት ለመሙላት ከኢትዮጵያ የፍትህ ህግ ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት ጋር እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።

ኮሚሽነር ዶክተር መኩሪያ ሃይሌ እንደገለፁት፤ የሲቪል ሰርቪስ ስራዎች ሪፎርሙን ውጤታማ ለማድረግ ከሚሰሩት ስራዎች መካከል የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ፕሮግራም አንዱ ነው።

የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች በሠራተኞችና ተቋማቱ መካከል ለሚኖረው አለመግባባት ቀልጣፋ ፍትህ በመስጠት በሀገራዊ ለውጡ የድርሻውን እንዲወጡ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር ፍርድ ቤት ዳኞች ያለባቸውን ውስንነት ለመፍታት ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ የፍትህ ህግ ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን አቅም ግንባታ ላይ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሲቪል ሰርቪስ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የአደረጃጀት፣ የመዋቅር ጥናትና ክለሳ እየተጠናቀቀ መሆኑን የገለፁት ደግሞ ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ስመኝ ውቤ ናቸው።

የሰቪል ሰርቪስ የአሰራር ስርዓቱን ለመለወጥ የሚያስችሉ መዋቅራዊ ለውጥ፣ የስራ አፈፃፀም ምዘናና የደረጃ ዕደገት አሰራር ጭምር ለማስተካከል እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

የሠራተኞች የስራ ብቃት፣ የደረጃ ዕድገት ውድድር፣ የአገልግሎት ማሻሻያ ስርዓትና ህጎች እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቁመው፤ ነፃ፣ ገለልተኛና ብቁ የሲቪል ሰርቫንት ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የፍትህ ህግ ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት የስልጠና አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ ታለ የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ዳኞች በፍትሐብሔርና በውሳኔ አፃፃፍ፣ በችሎትና በይግባኝ ውሳኔዎች ላይ ክህሎትና ግንዛቤ አግኝተው እንዲሰሩ ለማድረግ  የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም