በአማራ ክልል የተጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ ያመጣውን ውጤት የሚደግፍ ሰልፍ በዚገም ወረዳ ቅላጅ ከተማ ተካሄደ

5

ግንቦት 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ ዞን ዚገም ወረዳ በቅላጅ ከተማ በመንግስት የተጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ እያመጣ ያለውን ሠላምና እፎይታ የሚደግፍ ሰልፍ ተካሄደ።

ህዝባዊ ሰልፉ “ሠላማችን ለሁላችን” በሚል መሪ ሀሳብ የአገው ብሔረሰብና ምክር ቤቶች፣ አመራሮች፣ ወጣቶች፣ የሀይማኖት አባቶችና ተሳትፈውበታል።

ሰልፈኞቹ “እኛ ፊታችንን ወደ ልማት አዙረናል፤ አካባቢያችንን በተደራጀ መንገድ በመጠበቅ ለልማታችንን እና ለኑሮ ምቹ እናደርጋለን፣ ህግ ማስከበሩ የአንድ ሰሞን ስራ ሳይሆን ሁሌም በትኩረት ይፈጸም፣ መንግስት ህግ ሲያስከብር ወደልማት እንገባለን” የሚሉና ሌሎች ህገወጥነትን የሚያወግዙ እንዲሁም ሰላምና ልማትን የሚደግፉ መፈክሮችን አሰምተዋል።

የዚገም ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አድጓየሁ አያና ለሰልፈኞቹ ባስተላለፉት መልዕክት ባለፉት ዓመታት ህገወጥነት በመንገሱ በልማት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

ባለሀብቶች አካባቢውን ከማልማት ተቆጥበው ለመሸሽ የተገደዱበት ሁኔታ እንደነበር ገልጸዋል።

መንግስትና ህብረተሰቡ ህገወጥነት እንዲያበቃ ባሳዩት አቋም ሰላም ማረጋገጥ መቻሉን ጠቅሰው፤ ህገወጦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ህዝቡ ለሰላም ጥረቱ ድጋፉን ካጠናከረ አስተማማኝ ሰላም እንደሚሰፍን አረጋግጠዋል።

የአዊ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንግዳ ዳኛው በበኩላቸው ህዝቡን በመተማመን የተጀመረው የህግ ማስከበር ስራ ውጤታማ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም በተለያዩ የወንጀል ተግባራት ተሳትፈው ዞኑ በህግ ጥላ ካዋላቸው 1392 ተጠርጣሪዎች ውስጥ 118 ነፍሰ ገዳዮች ከዚገም መያዙን ጠቁመዋል።

አብዛኛው ወንጀለኛ የተያዘው በህብረተሰቡ ድጋፍና የሠላም ወገንተኝነት ነው ብለዋል።

ህዝቡ ሲተባበር የማይፈታ ችግር የማይመለስ የህብረተሰብ ጥያቄ አለመኖሩን አስረድተው፤ ድጋፉን ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

“ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ህዝብን ከህዝብ ጋር ሲያገናኙ የቆዩ መልካም እሴቶች መጠናከር አለባቸው” ያሉት ደግሞ የመተከል ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ፀኃይ ጎዩ ናቸው።

በመተከልና በአዊ ብሔረሰብ ዞኖች በሴረኞች ምክንያት ህዝባዊ ሠላም ርቆ ቢቆይም ህዝባዊ የሠላም ግንኙነት ከተጀመረ ወዲህ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ