ኢትዮጵያን የሚመስል የፀጥታ ተቋማት ግንባታ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

148

ግንቦት 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን የሚመስል የፀጥታ ተቋማት ግንባታ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የምስጋና እና ዕውቅና መርሐግብር ዛሬ በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ንግግር የሰላም ጊዜ በየአካባቢው በጦርነቱ በየግንባሩ ደፋ ቀና ለሚለው ፌዴራል ፖሊስ ቀን የእንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

ህዝብ ሰላም ውሎ የሚያድረው በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ልፋትና ተጋድሎ ነው ብለዋል።

የሰላምን ዋጋ ብንገነዘብ ወደ ግጭት አንገባም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለአገር ሰላምና ብልፅግና መሰረት ሰላም በመሆኑ የፀጥታ ተቋማትን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።

ፀጥታና ሰላም ለማረጋገጥ የሚጋደሉ ፖሊሶችን ማክበር ተገቢ ነው፣ አነስተኛ ደመወዝ እየተከፈላቸው ለአገር ከፍተኛ ዋጋ የሚከፍል ፖሊስ ነው ብለዋል።

የኛ ዓላማ በዕውቀት በዕውነት ለህዝብ የሚሰሩ ተቋማትን ማጠናከር ነው፣ የፀጥታ ተቋማትን የማጠናከር ስራ የፌዴራል ፖሊስ ምሳሌ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ 24 ሰዓት የሚሰራ ኃይል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ ንፁሃን ዜጎች ከተኩላዎች እንድትጠብቁ አሳስባለሁ ብለዋል።

ፖሊስን በማዘመን ታሪክ ራስ መኮንን ትልቅ ሚና እንደነበራቸው ገልፀው፣ ከአፄ ምኒልክ ጀምሮ እስከ አፄ ኃይለስላሴ ዘመን እየጎለበተ መምጣቱን ገልፀዋል።

ፖሊስ አገር በመጠበቅ ብቻ ሳይሆን በመንግስት ምስረታም ሚናው ጉልህ ነበር ብለዋል።

የቀደመ ታሪክ ላይ የዛሬ መሰረት ነው፣ኢትዮጵያን የሚመስል የኢትዮጵያ ፖሊስ መገንባት ግባችን ነው ብለዋል።

በማህበረሰቡ ዘንድ የሚከበር፣ ኢትዮጵያን የሚመጥን፤ የግዳጅ አፈፃፀም የተዋጣላትና ከፌዴራል ስርዓቱ ጋር የተናበበ ፖሊስ ተቋም ግንባታ ዕውን እንዲሆን ይሰራል ነው ያሉት።

የሚገነቡ ተቋማት ኢትዮጵያን በሰላም ማቆየት ብቻ ሳይሆን ለትውልድ የምትሻገር ኢትዮጵያን ግንባታ መሰረት መጣል ነው ብለዋል።

ፖሊስን የማጠናከር ስራችንን ይጠናከራል፣ ኢትዮጵያን የሚመስል የዘመነ ተቋም ግንባታው ተጠናክሮ ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም