አሸባሪው ሕወሓት ከፍቶት የነበረውን ጥቃት ለመመከት የፖሊስ ሰራዊት ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት አኩሪ ገድልና ጀግንነት ፈፅሟል

ግንቦት 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ሕወሓት በሰሜን ኢትዮጵያ ከፍቶት የነበረውን ጥቃት ለመመከት በተደረጉ ዘመቻዎች የፖሊስ ሰራዊት ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት አኩሪ ገድልና ጀግንነት ፈፅሟል።

'በመስዋዕትነታችን የአገራችን አንድነትና የህዝብ ሰላም ይረጋገጣል' በሚል መሪ ሀሳብ የምስጋና እና ዕውቅና መርሐግብሩ እየተካሄደ ይገኛል።

የፌዴራል ፖሊስ ሰራዊት ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል 80 ዓመት የሞላው የፖሊስ ተቋም በአገር ሕልውና ዘመቻዎች ከመከላከያና ከክልሎች ፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት አኩሪ ገድል ፈፅሟል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ባደረገው ሪፎርም በአፍሪካ ቀዳሚ የሚያደርገውን የቴክኖሎጂ ትጥቅ እየታጠቀ መሆኑን፣ የወንጀል ምርመራ አቅምና ብቃቱን ማሳደጉን ገልፀዋል።

በተቋሙ ተልዕኮ የላቀ ስራ አፈፃፀም የበለጠ ለማሳደግ ዕውቅና መስጠትና ምስጋና ማቅረብ የበለጠ ሞራል ስለሚፈጥር ዓመታዊ የፖሊስ ቀን መርሐ ግብሩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በዓውደ ግንባሮች ጀግንነት የፈፀሙ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የግልና የቡድን ጀግኖችና የስራ ክፍሎች የጀግናና የላቀ ጀግና ሜዳይ እና የሰርተፊኬት ዕውቅና የሚሰጣቸው ሲሆን በጦርነቱ የተሰው አባላትም ይመሰገናሉ ነው ያሉት።

የዛሬው መርሐ ግብር ማስጀመሪያ መሆኑን ገልፀው፤ በቀጣይም በክልል ጠቅላይ መምሪያዎቹ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። በመርሐ ግብሩ የኮሞሮስ፣ ታንዛኒያ፣ የጁቡቲ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የኬንያ ፖሊስ ተቋማት እና የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የፖሊስ ተቋማት መሪዎችም ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም