መንግስት ለማዕድን ሀብት የተለየ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው

252

ግንቦት 27 ቀን 2014 (ኢዜአ)  መንግስት የማዕድን ሀብትን ከየትኛውም ጊዜ በተለየ የዕድገት አማራጭነት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት መሆኑን ማዕድን ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በዋና መስሪያ ቤቱ ያቋቋመውን የማዕድን ጋለሪ ዛሬ አመሻሽ አስመርቆ ለጎብኚዎች ክፍት አድርጓል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ዲፕሎማቲኩ ማህበረሰብ፣ የዘርፉ አልሚዎችና ባለሀብቶች እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ ሚሊዮን ማቲዎስ የማዕድን ሀብት ዋነኛ የዕድገት አማራጭ በመሆኑ ከየትኛውም ጊዜ በተለየ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ነው ብለዋል።

ጋለሪው ዘርፉን የማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለው በመግለጽ ይህ ለባለሀብቶች የኢንቨስትመንት አማራጭ ማሳያ የሆነው ጋለሪ ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጓል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ማዕድን ጋለሪ የማዕድን መረጃን በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ ያከማቸ ሲሆን የጋለሪው ጎብኚዎች በኢትዮጵያ የሚገኙ የማዕድን ሀብቶች በዓይነትና በመገኛ ስፍራዎች በቀላሉ እንዲረዱ ያስችላል።

''ጋለሪውን የጎበኘ ኢትዮጵያዊ ዕውቀትና ቁጭትን ይዞ ይወጣል'' ያሉት አቶ ሚሊዮን፤ መጪው ጊዜ በተስፋ የተሞላ እንዲሆን ያደርገዋል" ብለዋል።

በምርምር ዘርፉም ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበረሰብም ጋለሪውን በመጎብኘት ስለ ማዕድናት ግንዛቤ እንዲጨብጡ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ጋለሪውን ለማደራጀት የማዕድን ዘርፍ ኩባንያዎች ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩት።

በዚህም በማዕድን ዘርፍ የተሰማሩና በጋለሪው መቋቋም አስተዋጽኦ ያደረጉ ኩባንያዎችም ዕውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

የማዕድን ጋለሪው ከተቋሙ የሪፎርም ስራ ውጤቶች መካከልም አንዱ ሲሆን ጋለሪውን ለማደራጀትም ግማሽ ዓመት እንደፈጀ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም