በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ቀርሳ ከተማ ዛሬ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ14 ሰዎች ህይወት አለፈ

3

ሐረር፣ ግንቦት 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ቀርሳ ከተማ ዛሬ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ14 ሰዎች ህይወት ማለፉን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሙኒኬሽን እና ሚዲያ ዲቪዥን ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ቶሎሳ ጎሹ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አደጋው የደረሰው ዛሬ ከቀኑ 8 ሰአት በከተማው ጫት ተራ በተባለው ስፍራ ነው።

አደጋውን ያደረሰው ከድሬዳዋ ወደ አዲስአበባ ሲሚንቶ ጭኖ ሲጓዝ የነበረው የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 B 28742 አአ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ መሆኑን ተናግረዋል።

የአደጋው መንስኤ አሽከርካሪው ፍሬን መቆጣጠር ባለመቻል ቁልቁለቱን ያለምንም ቁጥጥር ተምዘግዝጎ በስፍራው  ወደ ገበያ ይጓዙ የነበሩ 14 እግረኞችን ሊገድል ችሏል ብለዋል።

ህይወታቸው ካለፉት ስድስቱ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረው አሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ውሎ ምርምራ እየተካሄደበት መሆኑንም ገልፀዋል።

ከሟቾቹ በተጨማሪ ሁለት ከፍተኛ አደጋ የደረሰባቸው እግረኞች በድሬዳዋ ድል ጮራ ሆስፒታል ህክምና እየተሰጣቸው መሆኑን ዋና ኢንስፔክተር  ቶሎሳ አስታውቀዋል።

Description: ‼

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ