የሕግ ማስከበር ዘመቻው በሕግ የበላይነት ላይ ይታዩ ለነበሩ ክፍተቶች ምላሽ እየሰጠ ነው - የእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎች

83

እንጅባራ፣ ግንቦት 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሕግ ማስከበር ዘመቻው እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በአንጻራዊነት በሕግ የበላይነት ላይ ይታዩ ለነበሩ ክፍተቶች ምላሽ እየሰጠ እንደሆነ በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ ዞን የእንጀባራ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የዞኑ አስተዳደር ዘመቻውን አስመልክቶ ከእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ዛሬ ውይይት አድርጓል።
በውይይት መድረኩ አስተያየታቸው የሰጡ የከተማው ነዋሪዎች መንግስት የሕግ የበላይነትን እንዲያስጠብቅ ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበር ገልጸዋል።

መንግስት ሕግ ወደ ማስከበር እርምጃ መግባቱ የሕዝቡን ጥያቄ የመለሰ መሆኑን ገልጸዋል።

ሕግን ማስከበር የዘመቻ ብቻ ሳይሆን የዕለት ተለት ስራ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ዘመቻው ዘግይቶ የተጀመረ ቢሆንም ህዝቡ ሲጠይቅ የነበረውን የሰላም፣ የደህንነትና የሕግ የበላይነትን ክፍተቶች እየመለሰ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዊ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንግዳ ዳኛው በሕግ ማስከበር ዘመቻው በማታለል፣ በውንብድና፣ በዘረፋና በስርቆት የወንጀል ድርጊቶች የተጠረጠሩ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

"ዘመቻው ከጸጥታ አካላት ባለፈ በሰላም ፈላጊው ማህበረሰብ ይሁንታ፣ ተሳትፎና ድጋፍ እየተመራ ነው" ያሉት አቶ እንግዳ፤ ሕዝቡ ትብብር ማድረጉን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም