በሀዋሳ ከተማ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በአንድ ቢሊዮን ብር በጀት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ

243

ሀዋሳ፣ ግንቦት 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሀዋሳ ከተማ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በአንድ ቢሊዮን ብር በጀት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ገለጹ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ከንቲባው ከተማዋን ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ምቹ፣ ተስማሚና ተመራጭ ለማድረግ  የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል።

ዓመቱ በጣም ሰፊ ፕሮጀክቶች ይፈጸሙበታል ተብሎ የታቀደበት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ መንገድና የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግንባታ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶቹን በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ ተናግረዋል።

የልማት ስራዎቹ እየተከናወኑ ያሉት በከተማዋ ማስተር ፕላን  መሠረት መሆኑን ገልጸው፤ ይህም የከተማዋን ልማትና እድገት ለማፋጠን ያስችላል ብለዋል።

አዳዲስ በተፈጠሩ ሰፈሮች የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ለማዳረስ ትኩረት መሰጠቱን ያመለከቱት ከንቲባው፤ በተለይ በእነዚህ ቀበሌዎች ውስጥ የመንገድ ከፈታ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የሆስፒታልና የአስፓልት መንገድ ግንባታ  መገባደዱን  አስታውቀዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከተከናወኑ ዋና ዋና ስራዎች መካከል ከ100 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባውን የ15 ኪሎ ሜትር ዘመናዊ የመንገድ ዳር መብራት ዝርጋታን ጠቅሰዋል።

የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ዳር መብራት ዝርጋታ በማከናወን ለሀብረተሰቡ የረጅም ጊዜ  ጥያቄ ምላሽ መስጠት መቻሉን አውስተዋል።

እንዲሁም ማህበረሰቡን በማንቀሳቀስ 60 ሚሊዮን ብር የሚገመት ፓርክና የአረንጓዴ ልማት ተግባራት መከናወናቸውን አመላክተዋል።

በ12ቱ የከተማዋ ገጠር ቀበሌዎችም የኤሌክትሪክ መብራት ዝርጋታና የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት የማሻሻል ስራ መከናወኑን አብራርተዋል።

ከንቲባው አክለውም ከብልጽግና ጉባዔ በኋላ ከህዝቡ ጋር በመወያየት የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በልዩ ንቅናቄ እየተመራ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት ትላልቅ የፍሳሽ ግንባታ መጀመሩን አስታውቀዋል።

የመሰረተ ልማት አቅርቦት ስራዎች ለሀዋሳ ህዝብ ትልቅ ትርጉም እንዳላቸው ጠቅሰው፤ በተለያዩ መስኮች መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ምቹ መደላድል  እንደሚፈጥር አብራርተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም