አሸባሪው ሕወሓት በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙ 503 ትምህርት ቤቶች ማውደሙና መዝረፉ ተገለጸ

3

ደሴ፣ ግንቦት 27/2014.( ኢዜአ ) አሸባሪው ሕወሓት በደቡብ ወሎ ዞን በሚገኙ 503 ትምህርት ቤቶች ማውደሙና መዝረፉን  የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

በአማራ ክልል የወደሙና የተዘረፉ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

በደቡብ ወሎ ዞን ተንታ ከተማ የሚገኘው በሕወሓት ወረራ ጉዳት የደረሰበት “የአሰፋ ወሰን አልጋ ወራሽ” ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተመሰረተበት 75ኛ ዓመት የኢዮቤልዩ በዓልና የመልሶ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል።

የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ደረጀ አማረ እንዳሉት፤በዞኑ በሚገኙ 1 ሺህ 270 ትምህርት ቤቶች ከ400 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው።

ይሁንና ሕወሓት በዞኑ በፈጸመው ወረራ 503 ትምህርት ቤቶች ላይ ማውደሙንና መዝረፉን ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት በመማር ማስተማር ሂደቱ ችግር መፍጠሩን ተናግረዋል።

ውድመቱና ዝርፊያው በዞኑ ያሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች ምጣኔ ላይ አሉታዊ የሆነ ተጽእኖ ማሳደሩን አመልክተዋል።

ባለሃብቶች፣ድርጅቶች፣ ዳያስፖራውና ሕብረተሰቡ በመልሶ ማቋቋም ስራው እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመው  በመንግሥት ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ ትምህርት ቤቶችን ለመጠገን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተንታ ከተማ የአስፋ ወሰን አልጋ ወራሽ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ጥበቡ ተፈራ ሕወሓት በአካባቢው በቆየባቸው ጊዜያት ትምህርት ቤቱን የጦር ማዘዣ ጭምር አድርጎት እንደነበረና በዚህም ምክንያት የመማሪያ ሕንጻዎቹ መጎዳታቸውን አመልክተዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድወሰን አቢ በበኩላቸው በክልሉ በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ከአራት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች መውደማቸውንና መዘረፋቸውን ተናግረዋል።

የወደሙ ትምህርት ቤቶችን በተሻለ ደረጃ ለመገንባት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንና ለአስፋ ወሰን አልጋ ወራሽ ትምህርት ቤትም ከ560 ሺህ ብር በሚበልጥ ወጪ የወንበሮችና ጠረጴዛዎች ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቶችን በመጠገንና በማቋቋም የተጀመረው ጥረት ሁሉም ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ድጋፉን እንዲያደርግ  አቶ ወንድወሰን ጥሪ አቅርበዋል።

በአማራ ክልል የወደሙና የተዘረፉ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።