‘ኢትዮጵያ ታምርት’ ንቅናቄ የአገር ውስጥ ችግሮችንና ዓለማቀፍ ጫናዎች የሚቋቋም ኢንዱስትሪ እስከመፍጠር ይዘልቃል

4

ግንቦት 27/2014 (ኢዜአ) ‘ኢትዮጵያ ታምርት’ ንቅናቄ የአገር ውስጥ ችግሮችና ዓለማቀፍ ጫናዎች የሚቋቋም ኢንዱስትሪ እስከመፍጠር እንደሚዘልቅ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናገሩ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአገር ውስጥና በውጭ ጫናዎች እየተፈተነ ያለውን ኢንዱስትሪ መታደግ የሚያስፈልግበት ነባራዊ ሁኔታ መጥቷል።

በጦርነትና በተከሰተው በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ሳቢያ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ስራቸውን አቁመዋል፤ ቀሪዎቹም ማምረት ከሚገባቸው ከ50 በመቶ በታች እያመረቱ ነው ብለዋል።

በተለያዩ የአለም አገራት የሚደረጉ ግጭቶች ወደ ውጭ በሚላኩና ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጫና በማሳደሩ ኢትዮጵያንና መሰል በማደግ ላይ ያሉ አገራት ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው እንደሆነ እንደ ማሳያ ሊወሰድ ይችላል ይላሉ።

ኢትዮጵያ በነዚህና በሌሎች የተለያዩ ችግሮች ሳቢያ የተጎዳውን ኢንዱስትሪ በዘላቂነት ለማቋቋም ‘ኢትዮጵያ ታምርት’ የሚል ንቅናቄ መጀመሯን አስታውሰዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ‘ኢትዮጵያ ታምርት’ የሚለው ንቅናቄ በዓለም ላይ በሚያጋጥም ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮችና ማዕቀቦች የሚረበሸውን ኢንዱስትሪ ለመታደግና ዘላቂ እድገት እንዲኖረው ያግዛል።

”ኢትዮጵያ ጠንካራና ተወዳዳሪ አገር ሆና ውጫዊ ጫናዎችን ለመቋቋም ያላትን አቅም አሟጣ መጠቀምና ማምረት ያለባት ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል።

”ራስን መቻል የሉዓላዊነትና የክብር ጉዳይ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ ”በእጃችን ላይ ያለውን ሃብት ተጠቅመን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የምንቀይርበትን ንቅናቄ ጀምረናል” ነው ያሉት።

ንቅናቄው በ2022 ዓ.ም እንደ አገር የበጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ ለመተግበር ሰፊ እድል ይኖረዋልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ ጸጋ እና ሰፊ የሰው ኃይል እንዲሁም የተመቻቸ ፖሊሲ ቢኖራትም ይህንን ወደ ሃብት የመቀየርም ስራ ይቀራታል ነው ያሉት።

የ’ኢትዮጵያ ታምርት’ ንቅናቄ በኢንዱስትሪው ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን የአጭር ጊዜ ችግሮችን መፍታት ብቻ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ የሚያጋጥሙ ስጋቶችን መፍትሄ  እንዲሆን እየተሰራ ነው።

ኢትዮጵያ ያላትን ጸጋዎች በመጠቀም በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ኢንዱስትሪው አገራዊ የምርት ድርሻው ከ6 ነጥብ 9 በመቶ  ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ ለማሳደግ ግብ ተጥሏል።

አገሪቱ በ2022 ዓ.ም ከአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በዓመት ወደ ውጪ ከሚላክ ምርት አሁን ከሚገኘው 4 መቶ ሚሊዮን ዶላር ወደ 9 ቢሊዮን ዶላር ማሳደግ ዋነኛ ዓላማውም ነው።

በተጨማሪም የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የማምረት አቅም ወደ 85 በመቶ ማሳደግ እንዲሁም ከ5 ሚሊዮን ለሚልቁ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ነው የተወጠነው።

ከተጀመረ ጥቂት ወራት ያሳለፈው የ’ኢትዮጵያ ታምርት’ ንቅናቄ በርካታ ባለሃብቶች ወደ ስራ እየገቡ፤ ባለድርሻ አካላትም ተቀራርበው መስራት ጀምረዋል ብለዋል ሚኒስትሩ።

የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችን፣ ባለድርሻ አካላት፣ ሚዲያዎችና ሌሎችም ጉዳዮን ትልቅ አገራዊ አጀንዳ አድርገው በመንቀሳቀሳቸው በዘርፉ ትልቅ መነቃቃት ተፈጥሯል ነው ያሉት።

የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለመጨመር የሀይል አቅርቦት፣ የመሬት፣ የሥልጠና፣ የብድር አቅርቦትና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

አለማቀፍ ጫናዎች የሚቋቋም ኢንዱስትሪ እስከመፍጠር የሚዘልቀውን ንቅናቄ ተግባራዊነት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ሚኒስትሩ ጥሪ አቀርበዋል።