የምዕራብ አርሲ ዞን 67 ሰራተኞችን ከስራ አሰናበተ

137

ሻሸመኔ፤ ግንቦት 27/2014 (ኢዜአ)  የምዕራብ አርሲ ዞን በአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ፈጥረዋል ያላቸውን 67 ሰራተኞች ከስራ ማሰናበቱን አስታወቀ። 

የዞኑ ምክትል አስተዳደሪ አቶ  አሰፍ ቶሎሳ በዞኑ ባለው የመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ሕዝቡ ቀልጣፋና ፍትሐዊ አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻለ ገልጸዋል።

"ሕዝብን በእምነትና በታማኝት እንዲያገለግሉ በተለያየ ደረጃ የተቀመጡ ባለሙያዎች የተሰጣቸውን አደራ  ባለመወጣታቸው አስተዳደሩ እርምጃ ለመውሰድ ተገዷል" ብለዋል።

አስተዳደሩ በአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ፈጥረዋል ያላቸውን 67 ሰራተኞች ከስራ ማሰናበቱን አመልክተዋል።

100 ባለሙያዎችን ከተመደቡበት ቦታ የማንሳት፣660 ባለሙያዎች ላይ የደመወዝ ቅጣት፣306 ባለሙያዎች የመጀመሪያ ጽሑፍ ማስጠንቀቂያና ለ396ቱ ደግሞ ላይ ደግሞ የቃል ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ 1 ሺህ 529 ባለሙያዎች እርምጃ ተወስዶባቸዋል።

"ባለ ጉዳዮችም መብታቸውን በሕግ አግባብ ከማስከበር ይልቅ የእጅ መንሻ መስጠትን እንደ አማራጭ መፍትሔ መውሰዳቸው ችግሩን አባብሶታል" ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው ተገልጋዩ ሕብረተሰብ መብቱን በትክክለኛው መንገድ ሊጠይቅ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

ከቀበሌ እስከ ዞን የሚታዩትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ሕዝቡ መብቱን የሚያስጠብቅባቸው የተለያዩ የአሰራር መዋቅሮች እየተመቻቹ መሆናቸውን አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም