በኢትዮጵያ የመረጃ ነጻነት አፈጻጸምን ለማሻሻል የሚያስችል ስምምነት ተደረገ

132

ግንቦት 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የመረጃ ነጻነት አፈጻጸምን ለማሻሻልና በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት በተለያዩ ተቋማት መካከል ተደረገ።

የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመረጃ ነጻነት ህግ አፈጻጸምን አስመልክቶ  ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትና ከመገናኛ ብዙሃን ተወካዮች ጋር በቢሾፍቱ ከተማ እየመከረ ነው።

ስምምነቱ መረጃ መስጠት ያለባቸው አካላት ለመገናኛ ብዙሃን እንዲሰጡ እንዲሁም መረጃውን በአግባቡ የመጠቀም ሁኔታን ለማሻሻል እንደሚያግዝ ተገልጿል።

የመረጃ ነጻነትን አስመልክቶ ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለቻቸው አለም አቀፍ ስምምነቶች ቢኖሩም አፈጻጸም ክፍተት እንደሚስተዋል ነው በውይይቱ የተነሳው።

መረጃን ለመገናኛ ብዙሃን እንዲሰጡ የሚፈለጉ አካላት መረጃን ከመስጠት የመቆጠብና ፍላጎት የማጣት አዝማሚያ መኖሩ ተመላክቷል።

መረጃን የሚቀበሉ ባለሙያዎች ደግሞ ከአውድ ውጪም ጭምር መረጃውን ለራሳቸው በሚያመች መንገድ የመጠቀም ዘንባሌዎች የሚስተዋሉ መሆኑም ተጠቁሟል።  

በመሆኑም የሚስተዋሉ የአፈጻጸም ችግሮችን ለማሻሻል በትብብር መስራት እንደሚገባ የተገልጸ ሲሆን  ስምምነቱ መፍትሄ ለማምጣት ወሳኝ ነው ተብሏል።

ለዚህም በኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ በመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የሁሉም ክልል መንግስታትና የከተማ አስተዳደሮች የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ቢሮዎች መካከል በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተደርጓል።

ሆኖም የመረጃ ነጻነት አተገባበር ክፍተት የሚስተዋልበት ሆኖ በመገኘቱ ይህን ለማሻሻል በጋራ መስራት እንደሚገባ ተነስቷል።

Description: ‼

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም