በምስራቅ አፍሪካ ከውኃ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የኢኮኖሚ ምንጮች የመንከባከብ ስራ እየተሰራ ነው

5

ግንቦት 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ከውኃ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የኢኮኖሚ ምንጮች የመንከባከብና የማሳደግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ‘ብሉ ኢኮኖሚ’ ወይም ከውኃ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የኢኮኖሚ ምንጮች መንከባከብ፣ ማሳደግና መጠቀም ላይ ያተኮረ ስልጠና ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ለዘርፉ ሙያተኞች ሰጥቷል።

በናይሮቢ ኬኒያ ከግንቦት 22 እስከ 24 ቀን 2014 ዓ.ም በተሰጠው ስልጠና የውኃ፣ የውኃ አካላትና የውኃ ሀብቶችን በተለየ መልኩ መንከባከብና ማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው።

የኢጋድ ‘ብሉ ኢኮኖሚ’ አስተባባሪ ዶክተር እሸቴ ደጀን እንደሚሉት፤ ዘርፉ እ.አ.አ በ2019 ዓ.ም ተደራጅቶ ተቋማዊ መልክ እየያዘ ይገኛል።

ለአባል አገራቱ ስለ ብሉ ኢኮኖሚ አስፈላጊነትና ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም የማሳወቅ ስራ በስፋት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በቀጣናው የአምስት ዓመት የብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ የተነደፈ ሲሆን አባል አገራቱ የራሳቸውን አገራዊ ስትራቴጂ እንዲያዘጋጁ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ይህንኑ ስትራቴጂ ለማሳካት እንዲቻል ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር የሶስት ዓመት ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆኑንም አንስተዋል።

ከነዚህ ፕሮጀክቶች አንዱ በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን መካከል ያለው የባሮ-አኮቦ-ሶባት ተፋሰስ ልማት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሌላው በዚሁ ማዕቀፍ የሶስት ዓመት የፕሮጀክት ኮንትራት የተያዘለት ኢትዮጵያና ኬኒያ የሚጋሩት የኦሞ-ቱርካና ተፋሰስም ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ በአባል አገራቱ ትላልቅ የውኃ ዳርቻዎች የብዝሃ-ህይወት እንክብካቤና ዘላቂ መተዳደሪያ መፍጠሪያ ፕሮጀክትም በትግበራ ላይ እንደሆነ አብራርተዋል።

ዶክተር እሸቴ አክለውም ኢጋድ ብሉ ኢኮኖሚ ዘርፍ ‘ኢኮ ፊሽ’ ከተሰኘ አጋር አካል ጋር በመሆን በዘላቂ የአሳ ሀብት ልማት ላይም ይሰራል ብለዋል።

በጥቅሉ ብሉ ኢኮኖሚ የአሳ ሀብት ልማት፣ የውኃ ቱሪዝም፣ ከውኃ አካላት ጋር የሚያያዙ ማዕድናት ልማትና በውኃ ትራንስፖርት ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

በመሆኑም ዘርፉን የበለጠ ጥቅም ላይ ለማዋል አባል አገራቱ ‘ብሉ ኢኮኖሚን’ ተቋማዊ ማድረግ፣ ባህላዊ አሰራሮችን ማዘመንና አዳዲስ አካሄዶችን ማካተት፣ ቀጣናዊ አሰራሮችን መተግበርና ቀጣናዊ ትብብርና ትስስርን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

‘ኢኮ ፊሽ’ ፕሮግራም ኮሙኒኬሽን ኤክስፐርት አንደሪ ሮሳናንድሪያኒ፤ የአሳ ሀብት በቀጣናው ለበርካታ ዜጎች መተዳደሪያ፣ የገቢ ምንጭና የስራ ዕድል መፍጠሪያ ቢሆንም በዘመናዊና ሕጋዊ መንገድ ካልተመራ ሀብቱ ለከፍተኛ ጉዳትና ብክነት የሚዳረግ መሆኑን አንስተዋል።

በኢጋድ የብሉ ኢኮኖሚ ዘርፍ አመቻችነት በተለይም በባሮ-አኮቦ-ሶባት እና በቱርካና ሀይቅ ተፋሰስ ለሚገኙ አሳ አስጋሪዎች ስልጠናና ዘመናዊ አሳ ማስገሪያ መሳሪያዎች የማቅረብ ሂደቶች እንዳሉ ጠቁመዋል።

በኬኒያ ግብርና፣ እንሰሳትና አሳ ሀብት ሚኒስቴር የአሳና ውኃ ሀብት ዳይሬክተሩ ሮድሪክ ኩንዱ በበኩላቸው ኬኒያ በ’ብሉ ኢኮኖሚ’ ዘርፍ ብዙ ስራ እየሰራች ነው ብለዋል።

በተለይም ዘርፉ በመንግስት ተቋማት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ እንዳይሆንና ሕዝቡ ጋር እንዲደርስ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል።

ይህንንም ለማድረግ የኬኒያ መንግስት ፖሊሲ፣ ሕግና ተቋማትን ለዚህ የተመቹ የማድረግ ስራ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

Description: ‼

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ