ቢሮው በአፋር ክልል አሸባሪው ህወሓት ጉዳት ያደረሰባቸው ተቋማትን ለማቋቋሚያ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ቢሮው በአፋር ክልል አሸባሪው ህወሓት ጉዳት ያደረሰባቸው ተቋማትን ለማቋቋሚያ ድጋፍ አደረገ

ሰመራ ኢዜአ ግንቦት 26/2014 የደቡብ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት የደረሰባቸውን የትራንስፖርት ተቋማትን መልሶ ለማቋቋሚያ የሚያግዝ ከግማሽ ሚሊዩን ብር በላይ የሚገመት የቢሮ መገልገያ ቁሳቁስ ድጋፍ ዛሬ አደረገ።
ድጋፉን የደቡብ ክልል ለትራንስፓርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አማካሪ ለአፋር ከልል ትራንስፓርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አስረክበዋል።
የአፋር ክልል መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ሃበና በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት አሸባሪ ህወሓት በክልሉ ጉዳት ካደረሰባቸው ዘርፎች መካከል የትራንስፖርት ሴክተሩ አንዱ ነው።
የሽብር ቡድኑ በክልሉ 21 ወረዳዎች በሚገኙ የዘርፉ ተቋማት ላይ እስከ 200 ሚሊዮን ብር የሚገመት ጉዳት ማድረሱን አስረድተዋል።
ከዚህ ጉዳት ለማገገም በክልሉ መንግሥት በጀት ብቻ የሚቻል ባለመሆኑ ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት ባህላችንን በተግባር ማሳየት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ከዚህ አኳያ ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለክልሉ ህዝብ እያሳዩ ያሉትን ወገናዊ አጋርነት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ቢሮ ያደረገው ከግማሽ ሚሊዮን ብር ላይ የሚገመት የቢሮ መገልገያ ቁሳቁስ ድጋፍ ክልሉ በዘርፉ ከደረሰበት ውድመት መልሶ ለማቋቋም የሚያግዝ መሆኑን ገልጸው፤ ለድጋፉ በክልሉ መንግሥት ስም ምስጋና አቅርበዋል።
የደቡብ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አማካሪ አቶ ዘርፉ አጥናፉ የአፋር ህዝብ የሀገሩን ሉዕላዊነት ማስከበር የድርሻ የተወጣ ፅኑ ኢትዮጵያዊ ነው ብለዋል።
የደቡብ ክልል ሕዝብም በዚህ ሂደት ከወንድም ኢትዮጵያውያን ጋር በመሰለፍ ለሀገሩ ህልውና የሚጠበቅበትን ግዴታውን የተወጣና ይኸው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም በተጓዳኝ በሽብር ቡድኑ በአፋር፣ በአማራና በሌሎች አካባቢዎች የተጎዱ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።
በአፋር ክልል በሽብር ቡድኑ የተጎዱ የትራንስፖርት ዘርፍ ተቋማትን ወደ አገልግሎት ለማስገባት የሚያግዝ ከግማሽ ሚሊዮን የሚገመት የቢሮ መገልገያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ድጋፉ ወንበሮች፣ ጠረንጴዛዎችና የሰነድ መደርደሪያዎችና ሌሎች ተያያዥ የቢሮ መገልገያ ቁሳቁን የሚያካትት መሆኑን አቶ ዘርፉ ተናግረዋል