በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አስተማማኝ ሰላምና ደህንነትን ለማስፈን የተሰራው ስራ ውጤታማ ነው

5

ፍቼ ግንቦት 26/2ዐ14/ኢዜአ/—በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አስተማማኝ ሰላምና ደህንነትን ለማስፈን በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ጭምር የተከናወኑ ህግና ፀጥታ የማስከበር ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ክፈለው አደሬ እንደገለጹት በቅርቡ በተደረገ ህግና ፀጥታ ማስከበር ሥራ 233 የአሸባሪው ሸኔ ቡድን አባላት እጃቸውን ለፀጥታ ኃይሎች ሰጥተዋል።

በዞኑ ስድስት ወረዳዎች ለአንድ ወር ያህል የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፖሊስና ሚሊሺያ አባላት በቅንጀት ያካሄዱት ሸኔን በመደምሰና ፀጥታን የማስከበር ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በዚህም አሸባሪው ሸኔ መሽጐባቸው የነበሩ የዞኑ ቆላማና ገጠር ቀበሌዎች በአብዛኛው ከቡድኑ በማጽዳት፤ የተዘጉ መንገዶች እንዲከፈቱ፣ የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች ሥራ እንዲጀምሩ መደረጉን ገልፀዋል።

አሸባሪው ሸኔ በአካባቢው 88 ትምህርት ቤቶችን ማቃጠሉንና፣ 125 ትምህርት ቤቶች ተዘግተው 68ሺህ 2ዐዐ የሚጠጉ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጉን ጠቁመዋል።

እንዲሁም 65 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የኣካባቢው የጤና፣ የግብርና እና ሌሎች ተቋማት እንዲወድሙ ማድረጉን ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።

የተደረገው የተቀናጀ ህግን የማስከበርና ፀጥታን በማስፈን ሥራ እነዚህ ተቋማት ተመልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ የአካባቢው ህዝብ ሰላምና ደህንነት ተሰምቶት እንዲንቀሳቀስ ያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኦፕሬሽኑ በርካታ የቡድኑ አባላት ሲደመሰሱ፣ 233 አባላቱ ደግሞ ለፀጥታ ኃይሎች እጅ እንዲሰጡ፣ ከባድና ቀላል የጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ያስቻለ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በግራር ጃርሶ፣ ደገም፣ ኩዩ፣ ወረጃርሶና ደራ ወረዳዎች ቡድኑ መሽጐባቸው የነበሩ በርካታ ቦታዎች ከሸኔ መጽዳታቸው አስረድተዋል።

በህግና ፀጥታ ማስከበሩ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላምና ደህንነት አስተማማኝ ለማድረግ ህዝብን ያሳተፈ የሰላምና ደህንነት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በቡድኑ የጥፋት ተግባር በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮችን በነፃነት ለመተግበር እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

ይህንን ሁኔታ ቀድሞ ወደ ነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ የተለያዩ ስራዎች ህዝብና መንግሥት ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዞኑ የኩዩ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ደሣለኝ በበኩላቸው ለወራት በአካባቢያቸው ሰላምና ፀጥታ ተስተጓጉሎ መቆየቱን ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት በተደረገ የተቀናጀ ፀጥታና ህግ የማስከበር ሥራ በወረዳው ሁሉም ቀበሌዎች ሰላም ሰፍኖ ነዋሪዎች በነፃ መንቀሳቀስ ጀምረዋል።

ይህ የተቀናጀ ተግባር ለህብረተሰቡ ሰላምና ፀጥታን የሰጠ በመሆኑ ነዋሪው ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ የበኩሉን እያበረከተ እንደሆነም አስታውቋል።

በደራ ወረዳ በጉንዶ መስቀል ከተማ በንግድ ሥራ  የሚተዳደሩት አቶ ዋሲሁን በድሩ ከአካባቢያቸው ወደ ፍቼ ከተማ የሚወስደው መንገድ በፀጥታ ችግር በመዘጋቱ ለችግር ተዳርገው መቆየታቸውን ገልፀዋል።

በቅርቡም በተደረገ ህግና ፀጥታ የማስከበር ሥራ ሸኔ ተደምስሶ መንገዱ በመከፈቱ መደሰታቸውን ገልጸው፤ይህም  ማህበራዊ ግንኙነቶችን ለማከናወን የረዳ መሆኑን ተናግረዋል።

ከመንግሥት ጐን ተሰልፈው አሸባሪውና ተላላኪው ሸኔን በፅናት እንደሚታገሉ፤ አሁንም ለተገኘው ድል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልፀዋል።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ዳይሬክተር ኮማንደር አዳሙ አባተ ህዝቡ በአካባቢው ሰላም፣ ፀጥታና ልማት እንዲሰፍን በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ የጥፋት ኃይሎችን በበለጠ ቁርጠኛ ሆኖ  እንዲታገል አሳስበዋል።

የሀገር ሽማግሌዎችና እናቶች ልጆቻቸው ያልተገባ መስዋዕትነት እንዳይከፍሉ ውይይትና ምክክርን እንዲያስቀድሙ የማነፅ ሥራ ዓላማ አድርገው እንዲተገብሩም አስገንዝበዋል።

በአካባቢው ህግ እንዳይከበር፣ ሰላም እንዳይሰፍን የሚፈልጉ ቡድኖችን አጋልጦ በመስጠት የአካባቢውን ሰላም ማስከበር የያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት መሆኑንም አስረድተዋል።