የዋህግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ሃላፊነታቸውን ባልተወጡ አካላት ላይ የተለያየ እርምጃ ተወሰደ

4

ሰቆጣ፤ ግንቦት 26/2014 (ኢዜአ)፡ የህገ ወጥ ንግድንና ኮንትሮባንድን ለመከላከል በተደረገው እንቅስቃሴ ሃላፊነታቸውን ባልተወጡ አካላት ላይ እርምጃ መውሰዱን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አስታወቀ።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን  መደበኛ ጉባኤን ዛሬ በሰቆጣ ከተማ አካሂዷል።

የብሔረሰብ አስተዳደር ዞኑ ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ  አቶ ስቡህ ገበያው ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ የህገ ወጥ ንግድንና ኮንትሮባንድን ለመከላከል ኮማንድ ፓስት ተቋቁሞ እየተሰራ ነው።

ኮማንድ ፓስቱ በተቋቋመ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ  ህገ ወጥነትን ለመከላከል በተደረገው እንቅስቃሴ የህዝቡን ጥያቄ ሊመልስ የሚችል ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

የህገ ወጥ ንግድንና ኮንትሮባንድን ለመከላከል በተደረገው እንቅስቃሴ ለህገ ወጦች ተባባሪ በመሆን ሲሰሩ በነበሩ አመራሮች፣ የጸጥታ አካላትና በንግድ ፅህፈት ቤት  ሰራተኞች ላይ የተለያየ እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል።

በአጠቃላይ በ18 አመራሮች፣ የጸጥታ አካላትና ባለሙያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመው፤አራት አመራሮች ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉንና  ለሁለት አመራሮች ደግሞ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ተናግረዋል።

ሶስት የንግድ ፅህፈት ቤት ባለሞያዎች ከስራቸው መታገዳቸውን የገለጹት አቶ ስቡህ፤ ዘጠኝ የጸጥታ አካላት ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ ነው ብለዋል።

እስካሁን በተደረገው የህገ ወጥ ንግድን የመከላከል እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ ያሳየውን ትብብር በቀጣይም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ኮማንድ ፓስት ባለፉት 26 ቀናት ውስጥ  ለሽብር ቡድኑ ሊደርስ የነበረ ከ22 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብና ሌሎች ቁሳቁሶችን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉም ተመልክቷል።