የአፍሪካ ቀን መከበር አፍሪካውያን የጋራ እሴቶቻቸውን በማጠናከር አብሮነታቸውን ለማጎልበት ይጠቅማል

143

ግንቦት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአፍሪካ ቀን መከበር አፍሪካውያን የጋራ እሴቶቻቸውን በማጠናከር አብሮነታቸውን ለማጎልበት እንደሚጠቅም በኳታር የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፈይሰል አሊይ ገለጹ።

የአፍሪካ ቀን በዓል በኳታር ዶሃ የዲፕሎማቲክ ክለብ ከ30 በላይ የአፍሪካ አገሮች ሚሲዮን መሪዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት ትናንት አመሻሽ ላይ ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት አምባሳደር ፈይሰል የአፍሪካ ቀን መከበር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

“የአፍሪካ ቀን በዓል መከበር አፍሪካውያን ነጻነታቸውንና የጋራ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ በእጅጉ ይጠቅማል” ብለዋል።

አፍሪካውያን የጋራ እሴቶቻቸውን በማጠናከር አብሮነታቸውን ለማጎልበት እንደሚጠቀሙበትም አመልክተዋል።

በዓሉን በንግግር የከፈቱት በኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር አብደላህ ቢን ሃሰን አል ጃብር በበኩላቸው ኳታር ከአፍሪካ ጋር ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ጥብቅ ወዳጅነት እንዳላት አስታውሰዋል።

“ኳታር ግንኙነቱን አጠናክሮ ሁለንተናዊ ትስስሩን የማስቀጠል ልዩ ፍላጎት አላት” ብለዋል።

የአፍሪካ 2063 የልማት ግብን ለማሳካት ይቻል ዘንድ የአፍሪካ አገሮች ከተቀረው የአለም ክፍል ጋር የሚኖራቸውን ሁለንተናዊ ትስስር ማጠናከር አስፍላጊ እንደሆነ በመድረኩ ተገልጿል።

በዚህ ሂደት ኳታር በአፍሪካ የምትጫወተው አዎንትዊ ሚና ተጠናክሮ የሚቀጥል ለመሆኑ በርካታ ማሳያዎች አሉ ተብሏል።

በዝግጅቱ ላይ ተቀመጭነታቸውን በኳታር ዶሃ ያደረጉ የአፍሪካ አገራት ኤምባሲዎችና ዜጎቻቸው የተሳተፉ ሲሆን የኢትዮጵያ ኤምባሲም በቀጠር የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ማህበር ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያን የባህል አልባሳትን ቁሳቁሶችን ያቀረበ ሲሆን ባህላዊ ምግቦችን የማቅመስ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡና አፈላል ስነ ስርዓትም አካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም