ኢትዮ ቴሌኮም ለነቀምቴ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዲጂታል ቤተ መጻህፍት አደራጅቶ አስረከበ

2

ነቀምቴ ግንቦት 26/2014(ኢዜአ)—የኢትዮ ቴሌኮም ምዕራብ ሪጅን ለነቀምቴ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዲጂታል ቤተ መጻህፍት አደራጅቶ አስረከበ።

የሪጅኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙላቱ ጉደታ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት ተቋማቸው ለዲጂታል ቤተ መጻህፍቱ የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች በማሟላት ለትምህርት ቤቱ አስረክቧል፡፡

ዲጂታል ቤተ መጻህፍቱ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥና የመማር ማስተማሩን ሥራ ለማጠናከር ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለውም አክለዋል።

ለቤተ መጻህፍቱ 21 ኮምፒዩተሮችና ማተሚያ ማሽኖች፣ ወንበርና ጠረጴዛዎች እንዲሁም የተሟላና ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የኢንተርኔት አገልግሎት የገቡለት መሆኑን አቶ ሙላቱ አስረድተዋል።

ለተማሪዎችና መምህራን መሠረታዊ የኮምፒዩተር ሥልጠና በመስጠት ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር እንዲተዋወቁ ለማድረግም የሪጂኑ ሠራተኞች መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል፡፡

ተማሪዎች  መሠረታዊ  የሶፍት ዌር እውቀት ጨብጠው  ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በመተዋወቅና በቂ ኢንፎርሜሽን በማግኘት ተወዳዳሪ ሆነው እንዲገኙ ሪጁኑ ያለምንም ክፍያ ቤተ መጻህፍትን አደራጅቶ ማስረከቡ ነው የተገለፀው፡፡

በተመሳሳይ የዲጂታል ቤተ መጻህፍቱን በምዕራብ ወለጋ ዞን ለግምቢ ሃጫሉ ሁንዴሣ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ለሻምቡ አቢሼ ገርባ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታውን አጠናቀው ለማስረከብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን  ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

ለ3ቱ ትምህርት ቤቶች 35 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው መሣሪያዎች የተሟላላቸው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የነቀምቴ ከተማ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ ከበደ በበኩላቸው ኢትዮ ቴሌኮም  የዲጂታል ቤተመጻህፍትን ለትምህርት ቤቱ በማስገባት ተማሪዎች ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በመተዋወቅ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ ስላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

የነቀምቴ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ደረጀ በንቲም ኢትዮ ቴሌኮም በከፍተኛ ወጪ ዲጂታል ቤተ መጻህፍቱን አስገንብቶ በማስረከቡ የተሰማቸው ደስታ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

ትናንት ግንቦት 25 ቀን 2014ዓም የተከናወነው የዲጂታል ቤተ መጻህፍት ርክክብ ረጅም ታሪክ ላለው የነቀምቴ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማህበረሰብ ከፍተኛ ተነሳሽነት የፈጠረ መሆኑም ተገልጿል፡፡