የኢንቨስትመንትና የአምራች ኢንዱስትሪውን ማነቆዎች በማረም ከመስኩ የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግ ይገባል

3

ቡታጅራ፤ ግንቦት 25/2014 (ኢዜአ)፡ በደቡብ ክልል በኢንቨስትመንትና በአምራች ኢንደስትሪው ዘርፍ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለይቶ በማረም ከመስኩ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አሳሰቡ።

የደቡበ ክልል የ”ኢትዮጵያ ታምርት!” የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ንቅናቄ ፎረም ”በተቀናጀና ቀጣይነት ባለው የድጋፍ ማዕቀፍ አምራቿን ደቡብ  እንፈጥራለን” በሚል መሪ ሀሳብ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞንና ወረዳ አመራሮች ጨምሮ በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶች በተገኙበት በቡታጅራ ተካሂዷል።

በፎረሙ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ርስቱ ይርዳው እንዳሉት ክልሉ ለአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ቀዳሚና የልማት ዕድል ካለባቸው አካባቢዎች ተርታ የሚጠቀስ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁን ከመስኩ ማግኘት የሚገባውን ያህል ጥቅም ማግኘት እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

ከዘርፉ የሚገባውን ጥቅም ለማግኘት ያለውን ዕምቅ አቅም ከማስተዋወቅ፣ ከአገልግሎት አሰጣጥና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመፍታት ለውጥ ለማምጣት በትኩረት እንደሚሰራ  ጠቁመዋል።

ፎረሙ በኢንቨስትመንትና በአምራች ኢንደስትሪ ዘርፍ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለይቶ ለማረምና ከውይይቱ የሚገኙ ሀሳቦችን መነሻ በማድረግ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መዘጋጀቱን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

በክልሉ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የቴሌኮምና ፋይናንስ አቅርቦት ወሳኝ በመሆኑ ከዚህ አንጻር የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ተቋማቱ በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ችግሮችን ተቋቁመው ላለሙ ባለሀብቶች ምስጋና አቅርበዋል።

 ወደ ሥራ ያልገገቡ ባለሀብቶች ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡ አሳስበው፤ ”ይህ ካልሆነ ግን መሬቱ ለሌሎች አልሚዎች ይተላለፋል” ብለዋል።

የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሐልጌዮ ጂሎ በበኩላቸው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች  በኢንዱስትሪው ልማት ላይ በሚፈለገው ልክ እየተንቀሳቀሱ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት በማጠናከር የህዝቡን ዕለታዊ ፍጆታ ከማሟላት ባለፈ የአምራች ኢንዱስትሪው የግብዓት ፍላጎት ማሟላት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዚህም  የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ልማት ማፋጠንና በሀገራዊ የምጣኔ ሀብት ላይ  ከፍተኛ ድርሻ እንዲኖረው መስራት ይገባል ብለዋል።

ፎረሙ ወደ ስራ የገቡ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ችግሮች ለመፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከርና መፍትሄዎችን በጋራ ለማስቀመጥ ታስቦ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በኢንዱስትሪው ዘርፍ መነቃቃትን ለመፍጠር ”ኢትዮጵያ ታምርት!” የሚል ንቅናቄ  በክልሎች  እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።