መሬት በፍትሃዊነት ለአገር ልማት እንዲውል በዘርፉ የዳበረ ክህሎት ያለው ባለሙያ ማፍራት ይገባል

108

ግንቦት 26/2014/ኢዜአ/ መሬት የቅሬታ ምንጭ ከመሆን ይልቅ በፍትሃዊነት ለአገር ልማት እንዲውል በዘርፉ የዳበረ ክህሎትና ብቃት ያለው ባለሙያ ማፍራት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በመተባበር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልና ከፌደራል ተቋማት ለተውጣጡ ለመሬት ዘርፉ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የ45 ቀን ስልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የከተሞች ልማት ለአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት የማይተካ ሚና አላቸው፡፡

ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹና ተስማሚ ሆነው እንዲደራጁ የከተሞችን መሰረታዊ አጀንዳዎችን ማዕከል ያደረጉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ቅሬታዎችን በመፍታት መሬትን ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል የዳበረ ክህሎት ያለው የሰው ሀይል ማፍራት ይገባል ብለዋል፡፡

ይሄንንም ታሳቢ በማድረግ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከአንድ ሺህ በላይ ለሚሆኑ የከተማ መሬትና ፕላን ዘርፍ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡

ይሄም የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ስርዓት በማዘመን በከተሞች ከመሬት አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚታየውን ኢ-ፍትሃዊነት፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር መፍታት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ዋቅጋሪ ነጋሪ በበኩላቸው የመሬት ምዝበራ የከተሞች መሰረታዊ ችግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመሬትና መሬት-ነክ ንብረቶችን ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት ለመቆጣጠር በሙያው የበቃ፣ በስነ-ምግባሩ የተመሰገነ የሰው ሃይል ማፍራት ይገባል ብለዋል፡፡

የከተማ መሬት በፍትሃዊነት ጥቅም ላይ እንዲውል የዘርፉ ባለሙያዎችን ማሰልጠንና የሙያ ብቃት ምዘና እንዲወስዱ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከአስር ዓመት በፊት አንድ ሺህ የማይሞሉት ከተሞች ዛሬ ላይ ቁጥራቸው ከአራት ሺህ 450 በላይ መድረሱን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም