ፈጠራና ኢንዱስትሪን ማበረታታት እና ዘመናዊ ግብርናን በከተማ ማስፋፋት ትኩረታችን ነው - ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ

121

ገላን ግንቦት 26/2014/ኢዜአ/ ከመደበኛ የኢንቨስትመንት ልማት ባሻገር "ፈጠራና ኢንዱስትሪን ማበረታታት እንዲሁም ዘመናዊ የግብርና ስራን በከተማ ማስፋፋት ትኩረታችን ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ።

በፕሬዚዳንቱ፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤና በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር የተመራው የምክር ቤቱ አባላት የገላን አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክና ብረታ ብረት ፋብሪካ፣ ሆራ ትሬዲንግ የቡና ማቀነባበሪያ እንዲሁም ሜልባ ማተሚያ ፋብሪካን ጎብኝተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት "የኢንቨስትመንት ተቋማት ቁልፍ ስራ የሚሆነው የሀገሪቱን ልማትና ዕድገት ወደ ፊት ከማራመድ ባለፈ  ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠር ነው"።

ከመደበኛ የኢንቨስትመንት ልማት ባሻገር "ፈጠራና ኢንዱስትሪን ማበረታታት፣ ዘመናዊ የግብርና ስራ በከተማ ማስጀመር ብሎም ማስፋፋት ትኩረታችንን ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

በከተሞች በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ "ከተሞች አምራች መሆን አለባቸው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ለዚህም ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ያሉ የኢንቨስትመንት ተቋማት ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር አንፃር አበረታች እንቅስቃሴ ቢኖራቸውም በቴክኖሎጂ ሽግግርና ፈጠራ ላይ አሁንም ረጅም ርቀት ይቀራቸዋል ነው ያሉት።

ለዚህም የክልሉ መንግስት መሬትና የፋይናንስ አገልግሎት ምቹ ከማድረግ ባሻገር ሌሎች አሰራሮችን እየዘረጋ ይገኛል ብለዋል።

በኢንቨስትመንት ልማት፣ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን በስፋት በማሸጋገር ክልሉ ጥሩ ጅምር ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ከ10ሺህ በላይ የሚሆኑትን ወደ ኢንቨስትመንት ማሸጋገር መቻሉን ተናግረዋል።

ለባለሃብቶች የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከማመቻቸት ባለፈ  ልዩ የኢኮኖሚ ዞን መቋቋሙንም ገልጸዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው በኦሮሚያ ክልል የታየው ለውጥ ሀገራዊ ለውጡ ኢትዮጵያን መቀየር እንደሚችል ማሳያና ማረጋገጫ መሆኑን ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የክልሉን ግብርና ከመሰረቱ ለመለወጥና ለማዘመን እያደረገ ያለው ጥረት ለሌሎች አካባቢዎችም ምሳሌ መሆኑን በማከል።

"በተለይም በመስኖ ስንዴ፣ በወጪ ምርት የአቮካዶ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተቀርፀው ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ኢንሼቲቮች በተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መሆኑን አይተናል" ብለዋል።

የኢንቨስትመንት ተቋማትን ከማነቃቃትና ከማበረታታት አኳያ በመሬት አቅርቦት፣ በአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የፋይናንስና አሰራር ማሻሻያዎች ረገድ አበረታች ስራዎች መከናወኑንም ማረጋገጫ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በማስፋፊያ መሬት አቅርቦትና የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰራር በመዘርጋት አበረታች ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ያመለከቱት ደግሞ የሆራ ትሬዲንግ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ መላኩ ናቸው።

ድርጅታቸው በወጪ ምርት የቡና ማቀነባበሪያና ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ መገጣጠሚያን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ተሰማርተው እየሰሩ መሆኑን አንስተው፤ በዚህም ከ1ሺህ 200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

የገላን አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪያል ፓርክና የአዳማ ቆሮቆና የብረታ ብረት ፋብሪካ ባለቤት አቶ አብዱልሃኪም ሙሐመድ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በገላን አካባቢ ዘርፈ ብዙ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በ28 ሄክታር መሬት ላይ ግንባታ ማስጀመራቸውን ገልፀዋል ።

ፓርኩን ፈጥኖ ለማጠናቀቅና ወደ ስራ ለማስገባትም በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው የክልሉና የፌዴራል መንግስት እያደረጉላቸው ያለው ድጋፍ አበረታች መሆኑን አመልክተዋል።

በውጭ ምንዛሪ፣ መብራት፣ ውሃና ሌሎች የመሰረተ ልማት አቅርቦት ላይ አሁንም ክፍተትና ችግሮች እያጋጠሙ በመሆኑ መንግስት እያደረገ ያለውን እገዛ ማጠናከር ይኖርበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም