የተደረገልን አቀባበል አስደስቶናል-ተማሪዎችና ወላጆች

251

ጂንካ፤ግንቦት 26/2014(ኢዜአ)፡ በዩኒቨረሲቲው ማህበረሰብ የተደረገልን አቀባበል አስደሳችና በቀጣይ ያለምንም ስጋት በትምህርታችን ላይ ትኩረት እንድናደርግ የሚያስችለን ነው ሲሉ ለኢዜአ አስተያታቸውን የሰጡ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ተናገሩ።

የተማሪ ወላጆች በበኩላቸው የጂንካ ዩኒቨርሲቲና የአከባቢው ማህበረሰብ ላደረገላቸው አቀባበል አመስግነዋል።

ከአዲስ ገቢ ተማሪዎች መካከል ከአዲስ አበባ  የመጣው ዳንኤል ማሞ  እንደገለጸው አከባቢው ላይ የጸጥታ ስጋት እንዳለ ተደርጎ ሲሰራጭ በነበረው መረጃ ምክንያት ወደ ጅንካ ዩኒቨርስቲ ላለመምጣት ወስኖ እንደነበር አስታውሷል።

የጅንካ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጉን ሲሰማ ሀሳቡን በመቀየርና ከወላጆቹ ጋር በመመካከር  ሁኔታውን ደርሶ  ማየት ይሻላል በሚል መምጣቱን ተናግሯል።

ከአርባ ምንጭ ጀምሮ በየአከባቢው ያለው ማህበረሰብ ያሳየን ከልብ የመነጨ ፍቅርና አክብሮት  የተናፈሰው ወሬ መሰረተ ቢስ መሆኑን እንድረዳ አድርጎኛል ብሏል።

''ከዚህ ቀደም ጂንካ የፍቅር አከባቢ ዜጎች ተዋደውና ተፈቃቅረው የሚኖሩባት እንደሆነ በተደጋጋሚ እሰማ ነበር'' ያለው ተማሪ ዳንኤል፤  መጥቼም ያረጋገጥኩት ይህንኑ ብሏል።

በአከባቢው ሰላምና መረጋጋት የለም በሚል ለመቅረት ያሰቡ ተማሪዎች በአካባቢው ያለው  ሁኔታ እጅግ ሰላማዊ በመሆኑ ወደ ዩኒቨርሲቲው እንዲመጡና ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ጥሪ አቅርቧል ።

ከሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ የመጣችው ተማሪ በረከት ካሳሁን በበኩሏ ጂንካ የፍቅር አካባቢ እንደሆነ ስሰማ የነበረውን በአካል በመገኘት አረጋግጫለሁ ብላለች።

በመንገድ ላይ እንግልት እንዳይገጥማቸው ትራንስፖርት ተመቻችቶላቸው  ለተደረገላቸው አቀባበልም ዩኒቨርሲቲውንና የአከባቢውን ማህበረሰብ አመስግናለች።

የተደረገልን አቀባበል ያለምንም ስጋት በትምህርታችን ላይ ትኩረት እንድናደርግ የሚያስችለን ነው ስትል የገለጸችው ተማሪ በረከት፤ ''ጠንክሬ በመስራት በትምህርቴ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እተጋለሁ ብላለች

 ሌሎች ተማሪዎችም የመጡበትን አላማ ሳይዘነጉ ሙሉ አቅማቸውን ትምህርታቸው ላይ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግራለች

ከአለምገና ከተማ አዲስ ገቢ ልጃቸውን ወደ ዩኒቨርሲቲው ለማድረስ የመጡት አቶ ሱልጣን ሙስጠፋ በበኩላቸው በጂንካና አከባቢዋ እንዲሁም በተጓዙባቸው መንገዶች ላይ የተረጋጋና ሰላማዊ ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል።

አከባቢው ላይ ተፈጥሮ ከነበረው የጸጥታ ችግር አንጻር ስጋት የነበራቸው መሆኑን ገልጸው፤ በአካል መጥተው የተመለከቱት ግን አካባቢው ሰላማዊ መሆኑን ነው።

''ጉዟችንን ያለምንም ችግር አጠናቀን ልጆቻችንን ወደ ዩኒቨርስቲው ማድረስ ችለናል'' ያሉት አቶ ሱልጣን ዩኒቨርስቲውና የአከባቢው ማህበረሰብ ላደረጉላቸው ደማቅ አቀባበል አመሰግነዋል።

 ከሐረሪ ክልል ጊርና ከተማ ከ1 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ተጉዘው ልጃቸውን ለማድረስ መምጣታቸውን የሚናገሩት መምህር ግርማ ለገሰ በበኩላቸው በስጋት ውስጥ ሆነው ወደ ጅንካ መምጣታቸውን  ተናግረዋል ።

ለስጋታቸውም ቀደም ሲል በጂንካና አከባቢዋ  ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ መደፍረስን ተከትሎ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ይሰራጩ የነበሩ  መረጃዎች ምክንያቶች እንደነበሩ አስረድተዋል።

''ይህን ሁሉ ኪሎ ሜትር ስንጓዝ ያለምንም ችግር መጥተናል'' ያሉት መምህር ግርማ፤ ቦታው ላይ ከደረሱ  በኋላ አከባቢው ሰላማዊና የተረጋጋ ሆኖ ማግኘታቸውን አረጋግጠዋል።

በሀሰተኛ መረጃዎች መወዛገብ  እንደማያስፈልግ ገልጸው፤ በዚህ ምክንያት ወደ ኃላ ያሉ ተማሪዎች ካሉ ካለምንም ስጋት መጥተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ስሉ  ጥሪ አቅርበዋል።

ወደ ዩኒቨርስቲው የገቡ ተማሪዎችም ለመጡበት ዓላማ ቅድሚያ በመስጠት ዓላማቸውን  እንዲያሳኩ መክረዋል።

 የጂንካ ዩኒቨረሲቲ ትናንትና ዛሬ 3 ሺህ 290 አዲስ ገቢ ተማሪዎችን እየተቀበለ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም