አሸባሪው ህወሃት ከአንዳንድ የግብጽና ሱዳን ጀነራሎች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት ለመጀመር እየሰራ ነው

155


አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት ከአንዳንድ የግብጽና ሱዳን ጀነራሎች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት ለመጀመር እየሰራ መሆኑን አንድ የቀድሞ የአውሮፓ ዲፕሎማት አጋለጡ።

አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ እወርዳለሁ በሚል እሳቤ በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በማካሄድ ከፍተኛ ውድመት ፈጽሟል፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱ ከሌሎች የክልል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በጥምረት በፈጸሙት አኩሪ ተጋድሎ የቡድኑ ውጥን ቢከሽፍም፤ አሁንም ካለፈው ስህተቱ ባለመማር ለዳግም ወረራ እየተዘጋጀ መሆኑን የሚያመላክቱ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡

የሽብር ቡድኑ እኩይ ዓላማውን ለመፈፀም የኢትዮጵያን ህልውና ከማይፈልጉ ጠላቶች ጋር በመስራት ላይ እንደሚገኝም ነው የሚገለጸው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ቀደም "አሸባሪው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በፈጸመበት ወቅት የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ወታደሮች ተሳትፈዋል፤ አንዳንዶቹም በጦርነቱ ሞተዋል" በማለት መግለጹ ደግሞ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ አብነት ነው፡፡

የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉትና በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር የነበሩት ሲሞ ፓርቪያነን ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በከፍተኛ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ላይ የሚገኘው ህወሃት ሌላ ደም አፋሳሽ ጦርነት ለመክፈት ከግብጽና ሱዳን ድጋፍ እየፈለገ ይገኛል፡፡

በዚህም በተለይ አንዳንድ የካይሮና ካርቱም ጀነራሎች ከአሸባሪው ህወሃት ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ለማዳከም እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አሁን ላይ በርካታ የውጭ አገር ጋዜጠኞች፣ ታዛቢዎችና የኢትዮጵያ መንግስት አሸባሪ ቡድኑ በርካታ ቁጥር ያላቸው ታጣቂዎቹን በአፋርና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች እያሰፈረ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ የሽብር ቡድኑ ለሌላ አውዳሚ ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን የሚያመላክቱ በርካታ አስረጂዎች አሉ፡፡

የሽብር ቡድኑ በስፋት ታጣቂዎችን ከመመልመል ባሻገር ከአንዳንድ የግብጽና ሱዳን ጀነራሎች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋትን ለመፍጠር እየሰራ ነው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተቀመጠለት እቅድ እየተከናወነ መሆኑ ደግሞ ውጫዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ከሽብር ቡድኑ ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ አድርጓል ይላሉ፡፡

ምንም እንኳ ግድቡ አሁን ላይ ኃይል መስጠት ቢጀምርም ግብጽና ሱዳን ከአንዳንድ ምዕራባዊያን የሚያገኙትን ድጋፍ በመጠቀም በግድቡና በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ላይ ያላቸውን ዓላማ ለማስፈጸም እየሰሩ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ የወልቃይት ጠገዴ ኮሪደር አሸባሪው ህወሃት ከግብጽና ሱዳን ድጋፍ ለማግኘት እጅጉን የሚፈልገው ስትራቴጂካዊ አካባቢ ነው፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን ይህን በመገንዘብ ነቅተው ሊቆሙ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡አሸባሪ ቡድኑ ለሰብዓዊ ድጋፍ ተብሎ ወደ ትግራይ ክልል የገቡ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለጦርነት እንደሚጠቀምም ነው ያነሱት፡፡

አሸባሪው ቡድን የኢትዮጵያን ህልውና የማይፈልጉ ጠላቶች ተላላኪ መሆኑን በተግባር እያሳየ እንደሚገኝ አንስተው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ የትኛውንም ሴራ የመመከት አቅም እንዳላት ያላቸውን አምነት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለምእራባዊያን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላት አገር መሆኗን የሚናገሩት ዲፕሎማቱ፤ ከዚህ አኳያ የምእራባዊያን አገራት በኢትዮጵያን ያለውን ትክክለኛ ሁኔታ በመገንዘብ ሊደግፏት ይገባል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም