የፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ለኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት የከፈለው ዋጋ ዘወትር በታሪክ የሚወሳ ነው

132

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ለኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት የከፈለው ዋጋ ዘወትር በታሪክ የሚወሳ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በተግባር ተፈትነው የተሻለ የአመራር ብቃት ላሳዩ 55 ፖሊስ መኮንኖች የስትራቴጂክ አመራሮች የማዕረግ እድገት ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እንዳሉት፤ በያዙት ማዕረግ ከአራት ዓመት በላይ ያገለገሉ፣ አርዓያ የሚሆን ፖሊሳዊ ስብዕና ያላቸው መኮንኖች ተለይተው የማዕረግ እድገት አግኝተዋል፡፡

የማዕረግ እድገት ከተሰጣቸው የፖሊስ መኮንኖች መካከል ከቤንሻንጉል ጉሙዝና አፋር ክልሎች ሁለት የረዳት ኮሚሽነርነት ማግኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የማዕረግ እድገት ያገኙ የፖሊስ መኮንኖች አገራቸውን ለማዳን ቀድመው የተገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያን ለማገልገል አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኘውን ወርቃማ እድል ለውጤት ለማብቃት ጥበብና አስተውሎት የተመላበት መስዋዕትነት መክፈል ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ ላይ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚሰነዘረውን ጥቃት ለመመከት ከሌሎች የጸጥታ ሀይሎች ጋር ተባብሮ መስራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የፖሊስ አገልግሎት ህብረተሰቡ በሚፈልገውና በሚጠብቀው ልክ በተሟላ ስነ ምግባርና በአገራዊ ፍቅር እየጎለበተ መሄድ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን ህዝብ የሚመጥን የሰላም አውድ ለመፍጠር አሁን ካለበት አቅም በበለጠ መስራትና መረባረብ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኢትዮጵያን የማረጋጋት አቅምና ልምድ ቢኖረውም ከጸረ ኢትዮጵያ ሀይሎች ፍላጎት አንፃር ተጨማሪ ስራ ማከናወን ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የፖሊስ ሰራዊት ዘመናዊ አሰራርን ታጥቆ ግዳጁን በብቃት መወጣት እንዲችል መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡

የማዕረግ እድገት የተሰጣቸው የፖሊስ መኮንኖች በበኩላቸው የኢትዮጵያ ህዝብ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ ዛሬም እንደትናንቱ ተግተን እንሰራለን ብለዋል፡፡

ፖሊስነት ከራስ በፊት ለህዝብና ለሀገር በመሆኑ ማንኛውንም መስዋዕትነት ከፍለን የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት እውን እናደርጋለን ብለዋል፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፊት የማዕረግ ዕድገት ከተሰጣቸው መኮንኖች መካከል 12ቱ የምክትል ኮሚሽነርነት 43ቱ ደግሞ ኮሚሽነርነት ማዕረግ ያገኙ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም