በአማራ ክልል ከ6 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት በዘመቻ ሊሰጥ ነው

114

ባህር ዳር ግንቦት 25/2014(ኢዜአ) በአማራ ክልል ከ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ለሚበልጥ ህዝብ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት በዘመቻ እንደሚሰጥ የክልሉ ጤና ቢሮ ዛሬ አስታወቀ።

በቢሮው የክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ማሞ በሰጡት መግለጫ ኮቪድ-19 በዓለማችንም ሆነ በኢትዮጵያ እየቀነሰ የመጣ ቢመስልም፤ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት አልተቻለም ብለዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የአፍና አፍንጫ ጭምብል ከማድረግ፣ እጅን መታጠብና ሌሎች የመከላከያ መንገዶችን ከመተግበር ባሻገር፤ ክትባት መስጠት ዋነኛ መፍትሄ ተደርጎ መወሰዱን አስረድተዋል።

በዚህም በክልሉ የኮቪድ-19  ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት በክልሉ ከሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአሥር ተከታታይ ቀናት  በዘመቻ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

ለክትባት ዘመቻው ውጤታማነት የግብዓቶች አቅርቦትና ስርጭት፣ የጤና ባለሙያዎች የማዘጋጀት  ስራዎች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

በዘመቻው ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመከተብ መታቀዱን አቶ ወርቅነህ ተናግረዋል።

ክትባቱም በጤና ተቋማትና ህዝብ በብዛት በሚገኝባቸው ሥፍራዎች፤ በትምህርት ቤቶች፣ በማረሚያ ቤቶችና ተፈናቃይ ወገኖች ባሉባቸው መጠለያ ጣቢያዎች የክትባት መስጫ ማዕከላት በማቋቋም ይሰጣል ብለዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚካሄደው የክትባት ዘመቻ ህብረተሰቡ በመከተብና ሌሎች እንዲከተቡ በመቀስቀስ ትብብር እንዲያደርግ አሳስበዋል።

እንዲሁም የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ባለድርሻ አካላት ክትባቱን ለማሳካት ድርሻቸውን እንዲወጡ አስተባባሪው ጠይቀዋል።

በተመሳሳይ የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ  በክትባቱ አሰጣጥ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በኮምቦልቻ  ከተማ እየተወያየ ነው።

የመምሪያው በለኃላፊ አቶ ጌታቸው በለጠ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በዞኑ ክትባት  ከ800 ሺህ ለሚበልጥ ሕዝብ እንደሚሰጥና ለዚህም ከ27 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎችና በጎ ፈቃደኞች ዝግጁ ናቸው።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን በበኩላቸው ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ክትባቱን እንዲወስድ ማድረግ ከሁሉም እንደሚጠበቅ አሳስበው፣ የዞኑ አስተዳደር ውጤታማ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ብለዋል።

በክልሉ በቅርቡ በተካሄደው ሁለተኛው ዙር የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ህዝብ መከተቡን ከቢሮው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም