ዩኒቨርሲቲ በምርምር ባወጣቸው ምርጥ የአትክልትና የሰብል ዝርያዎች ተጠቃሚ መሆናቸው አርሶ አደሮች ገለጹ

110

ሐረር ግንቦት 26/2014(ኢዜአ)የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ያወጣቸውን የተሻሽሉ ምርጥ የአትክልትና የሰብል ዝርያዎችን ተጠቅመው ምርታማነትን በማሳዳግ ተጠቃሚ መሆናቸውን አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች ተናገሩ።

ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ ከ18 ሺህ በላይ አባወራ አርሶ አደሮች በምርጥ ዘርና በተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጿል።

ዩኒቨርሲቲው የአካባቢው አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች ትኩረቱን የማህበረሰብ ተሳትፎንና ተጠቃሚነትን ላይ ያደረገ የውይይት መድረክ  ትናንት አዘጋጅቷል።

በዩኒቨርሲቲው በምርምር የተገኙ የሰብል፣ አትክልተና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች በአውደ ርዕይነት ለታዳሚው ቀርበዋል።

በምሰራቅ ሐረርጌ ዞን የባቢሌ ወረዳ አርሶ አደር ሙባረክ ወዚር እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በምርምር ያወጣቸው ምርጥ የአትክልትና ሰብል ዝርያዎች በሽታና የዝናብ እጥረትን ተቋቁመው የተሻለ ምርት በመስሰጠት አርሶ አደሩን የሚጠቅሙ ናቸው።

በተለይ ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት ያሰራጨው የስንዴ ዝርያ በሽታንና የዝናብ እጥረትን ተቋቁሞ በሄክታር እስከ 46 ኩንታል ምርት አንደሰጣቸው ጠቅሰው ይህም ቀደም ሲል ይጠቀሙበት ከነበረው ዝርያ በእጥፍ ብልጫ ማሳየቱን ተናግረዋል።

''ዩኒቨርሲቲው የሚያቀርብልን የተሻሻሉ የሽንኩርትና የድንች ምርጥ ዘሮች ከፍተኛ ምርት እንድናገኝ እያስቻለን ነው'' ያሉት የሐረማያ ወረዳ  የኩሮ ጃለላ ቀበሌው አርሶ አደር አህመድ መሐመድ ናቸው።

በተለይ በአሁኑ ወቅት ከዩኒቨርሲቲው የምናገኘው ''ቡቡ'' የተሰኘው የድንችና ሌሎች የአትክልት ዝርያዎች በአጭር ጊዜ የሚደርሱና በመጋዘን ቢቀመጡም የማይበላሹ በመሆናቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

በአፍረን ቀሎ ዩኒዬን ህብረት ስራ ማህበር የእፅዋት ሳይንስ ባለሙያ አቶ መሐመዲን አብዲ በምርጥ ዘር አቅርቦትና ማስፋፋት ጋር በተያያዘ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅርበት በመሥራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዩኒየኑ በተለይ ዩኒቨርሲቲው በምርምር ያወጣቸውን የበቆሎ፣ የማሽላ፣ የቦሎቄ፣የድንችና ሌሎች የሰብል ዝርያዎችን በዞኑ አምስት ወረዳዎች እያባዛ መሆኑን ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ስርጸት ቡድን መሪ አቶ ፈይሳ ሁንዴሳ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው  ምርታማነትን ለማጎልበት በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች፣ በሐረሪ ክልልና ድሬዳዋ አስተዳደር በሚገኙ  የምርምር ተቋማትና በአርሶ አደር ማሳዎች ላይ ቴክኖሎጂ የማስፋፋት  ሥራ ያከናውናል።

ዘንድሮም  ዩኒቨርሲቲው በምርምር ያሻሻላቸውን 95 የሰብል፣የአትክልት፣እንሰሳት፣ተፈጥሮ ሃበት ጥበቃና  ሌሎች  ቴክኖሎጂዎች ለአርሶ አደሩ ማድረሱን ተናግረዋል።

በተለይ በዘንድሮ የተሰራጩት 2ሺህ 500 ኩንታል በመስኖ የሚለማ የስንዴ ምርጥ ዘርን ጨምሮ የድንች፣ቦሎቄና ሌሎች  የሰብል ዝርያዎች  ድርቅና የዝናብ እጥረት ተቋቁመው ምርት ይሰጣሉ ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከ18 ሺህ በላይ አባወራ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመድረኩ የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ ተመራማሪዎች፣ ተማሪዎች፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ አርሶ አደሮችና ተጋባዥ እንግዶች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም