ግብርናውን ለማዘመን 17 ኢንሼቲቮች ተመርጠው እየተተገበሩ ነው - ርዕስ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ

146

ሞጆ፣  ግንቦት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) ግብርናውን ለማዘመን 17 ኢንሼቲቮች ተመርጠው እየተተገበሩ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ።

በኦሮሚያ ክልል ርዕስ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ እንዲሁም በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የተመራ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላትን ያቀፈ ልኡካን ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም እየተዘጋጀ ያለውን የችግኝ ጣቢያዎችን ጎብኝተዋል።

ከአረንጓዴ አሻራው ፕሮግራም የዝግጅት ቦታ ጉብኝት በፊት ለወጪ ምርት ታስቦ እየተዘጋጀ ያለውን የአቮካዶ ችግኝ ጉብኝት ተከናውኗል።

በምስራቅ ሸዋ ዞን ሞጆና ሉሜ ወረዳ አካባቢ በተካሄደው በዚሁ ጉብኝት ወቅት ርዕስ መስተዳድር ሽመልስ እንደገለፁት ለአገሪቱ እድገት ወሳኝ የሆነውን ግብርናን ማዘመን ጊዜው የሚፈልገው ስራ ነው።

"በተለመደው አሰራር ማስቀጠል የምንችለው ድህነትን ብቻ ነው" ያሉት አቶ ሽመልስ፤ የክልሉን ግብርና ለማዘመንና ከመሰረቱ ለመለወጥ ሰፊ ጥናቶች ተካሂደውና ወደ 17 የሚሆኑ መርሃ ግብሮች (ኢንሼቲቮች) ተመርጠው እየተሰሩባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ከነዚህ ውስጥ ዘጠኝ ኢንሼቲቮች ተቀርፀው እየተተገበሩ መሆናቸውን የተናገሩት ርዕስ መስተዳድሩ፤ ከእነዚህ ውስጥም በአሁኑ ወቅት 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን የቡና ችግኝ በክላስተር ለማልማት የዝግጅት ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።

በአጠቃላይ በቡና ኢንሼቲቩ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን በላይ የቡና ችግኞች የተተከሉ ሲሆን በተመሳሳይ የሻይ ልማት ላይ በምዕራብ ኦሮሚያ ሁሉም ዞኖች ላይ እየተሰራ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት 17 ሺህ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ለአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ መሰራጨቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይ 20 ሺህ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን ለማሰራጨት መታቀዱንም አክለዋል።

በዘንድሮው ዓመት ከ600 ሺህ ሄክተር በላይ ስንዴን በመስኖ ማልማት መቻሉን የገለፁት አቶ ሽመልስ፤ በመጪው የበጀት ዓመት ከ1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

የቢራ ገብስ ልማት በክልሉ በስፋት በመከናወኑ ከውጭ ይገባ የነበረውን የቢራ ብቅል በሀገር ውስጥ የገብስ ምርት መተካት መቻሉንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የቡና፣ የሻይ፣ የሙዝ፣ የማር ልማት፣ የገጠር ፋይናንስ አገልግሎት፣ የደን ልማት፣ የአቮካዶ፣ የእርሻ ሜካናይዜሽን እና ሌሎችም የግብርና ተግባራት በቴክኖሎጂ መደገፍ ከተቀረፁት ኢንሼቲቮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፣ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት፣ የስራ ዕድል ፈጠራና ምርቶችን  በብዛት፣ በጥራትና በፍጥነት ማምረት ዋነኞቹ ግቦች እንደሆኑም ነው አቶ ሽመልስ የተናገሩት።

ለመጪው ክረምት ከ4 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ችግኞችን ለመትከል እስከ አሁን ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን የጓድጓድ ዝግጅት መጠናቀቁንም ጨምረው ገልጸዋል።

በዋናነት የግብርና ዘርፉን ከመሰረቱ ለመለወጥ በሚደረገው በዚህ ጥረት ታዲያ የምክር ቤቱ ዕገዛ፣ ክትትልና ድጋፍ ካልታከለበት የተፈለገውን ውጤት ማምጣት እንደማይቻል ነው የገለጹት።

ለዚህም ምክር ቤቱ ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ዕገዛ ሊያደርግልን ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው  በምስራቅ ሸዋ ዞን ያየናቸው የአቮካዶ ችግኝ እና የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ዝግጅት የልማት ስራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው ብለዋል።

ሀገሪቱን ከድህነት ለማውጣት መንግስት ያስቀመጣቸው የልማት ዕቅዶች "በተጨባጭ መሬት ላይ እየተተገበረ መሆኑን በተግባር አይተናል" ያሉት ምክትል አፈጉባዔዋ፤ ሌሎች ክልሎችም አርአያውን ሊከተሉ ይገባል ብለዋል።

በጉብኝቱም በቀጣዩ በጀት ዓመት በምክር ቤታችን ለዘርፉ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ለማድረግ የሚያስችሉ ግብዓት አግኝተንበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም