የደሴ ፍኖተ-ሕይወት መረዳጃ እድር ከ1ሺህ 500 በላይ መጻሕፍትን ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት አበረከተ

47

ግንቦት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የደሴ ፍኖተ-ሕይወት መረዳጃ እድር ከአባላቱና ከተለያዩ ግለሰቦች ያሰባሰበውን ከ1ሺህ500 በላይ መጻሕፍትን ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት አበረከተ።

ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት “ሚሊዮን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል መሪ ኃሳብ ለአንድ ወር መጻሕፍትን ለማሰባሰብ የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ተቋማትና ግለሰቦች ምላሽ እየሰጡ ነው።

ይህንንም ተከትሎ የደሴ ፍኖተ ሕይወት መረዳጃ እድር ከአባላቱና ከተለያዩ ግለሰቦች ያሰባሰበውን ከ1 ሺህ 500 በላይ መጻሕፍትን ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት በዛሬው ዕለት አስረክቧል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ድጋፉን ተቀብለዋል።የዕድሩ ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን ማንደፍሮ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የተሻለች አገር ለመፍጠር አንባቢ ትውልድ ማፍራት ወሳኝ ነው።

ይህ አገራዊ ዓላማ እንዲሳካ እኛም የበኩላችንን አሻራ ለማሳረፍ ያሰባሰብነውን ከ1 ሺህ 500 በላይ መጻሕፍት አበርክተናል ነው ያሉት።

መጻሕፍቱ የተለያዩ ይዘት ያላቸውና ወቅቱን የዋጁ ናቸው ተብሏል።ዕድሮች ለህዝቡ የበለጠ ቅርብ መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ ዘሪሁን ይህንን ቅርበታቸውን በመጠቀም በጎ ዓላማዎች ላይ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

“የዕድሮች ሥራ ከመቀባበር ያለፈ ሊሆን ይገባል” ያሉት ሰብሳቢው ለትውልድ የሚበጅ ተግባር ማከናወን እንደሚኖርባቸውም ነው አጽንኦት የሰጡት።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው በጦርነት ብዙ ፈተና ካየችውና ችግሮችን ተቋቁሞ ማለፍ ምሳሌ ከሆነችው ደሴ ከተማ መጻሕፍት ለማበርከት እዚህ በመገኘታችሁ ለኛ ልዩ ትርጉም አለው ሲሉ ገልጸዋል።

ዛሬ ያደረጋችሁት ድጋፍ ብዙ ሰዎች ስለ ዕድር ያላቸውን ግንዛቤ የቀየረ ነው ያሉት ዲያቆን ዳንኤል ከአከባቢያችሁ እንዲሁም ከአባላቶቻችሁ በማሰባሰብ ለትውልድ ስጦታ ማበርከታችሁ ከአባቶች የሚጠበቅ ትልቅ ተግባር ነው ብለዋል።

ለትውልድ ማውረስ የሚገባው ቂምና በቀልን ሳይሆን እውቀት፣ ማስተዋልና መልካም ነገር ነው ያሉት አማካሪው እናንተ ይሄንን በተግባር በማሳየታችሁ ልትመሰገኑ ይገባል ሲሉም አክለዋል።

ገና ከጦርነት በአግባቡ ካላገገመችው ደሴ ከተማ መጻሕፍት ለማበርከት እዚህ ድረስ መምጣታችሁ ኢትዮጵያዊያን ወደ ፊት ማየት የሚችሉ ሕዝቦች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት የሚደረገው ድጋፍ መቀጠሉን የተናገሩት ዲያቆን ዳንኤል ተጨማሪ አካላት ድጋፍ ማድረግ እንዲችሉ ድጋፍ ማድረጊያ ቀነ ገደብ ለአንድ ሳምንት መራዘሙን ተናግረዋል።