የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ከ200 በላይ መስማት ለተሳናቸው ሴቶች የስራ እድል የሚፈጥር ፕሮጀክት ይፋ አደረገ

72

ግንቦት 26/2014 (ኢዜአ)  የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) በአዲስ አበባ ከ200 በላይ መስማት ለተሳናቸው ሴቶች የስራ እድል የሚፈጥር ፕሮጀክት ይፋ አደረገ።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ መንግስት ጉዳይ አስፈጻሚ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰንና የዩኤስኤይድ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሲን ጆንስ ፕሮጀክቱን ይፋ አድርገዋል።

ለሶስት ዓመት በሚቆየው ፕሮጀክት ‘ተኪ’ የወረቀት ቦርሳ አምራች ድርጅት ከአሜሪካ መንግስት በሚያገኘው የ550 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽንና የግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር የፕላስቲክ ቦርሳዎችን በማምረትና በማሰራጨት ለ200 መስማት የተሳናቸው ሴቶች የስራ እድል ይፈጥራል።

የወረቀት ቦርሳዎችና የፕላስቲክ ቦርሳዎችን መተካት የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል እንዲሁም በፕሮጀክቱ የአካል ጉዳተኞች መብትና አካታችነት ያለውን ግንዛቤ ለማሻሻል አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ገልጿል።

ዩኤስኤይድ ከተኪ የወረቀት የቦርሳ ድርጅት ጋር ያለው ትብብር አሜሪካ በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች አካታችነት፣ የአካባቢ ጥበቃና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ብሏል።

ዩኤስኤይድ እ.አ.አ በ2021 ለኢትዮጵያ ከ1 ጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉም ተገልጿል።

መስማት በተሳናቸው ሴቶች የሚንቀሳቀሰው ‘ተኪ’ የወረቀት ቦርሳ አምራች ድርጅት ከተመሰረተ ከስድስት ዓመት በላይ አስቆጥሯል።

ድርጅቱ በአሁኑ ሰአት 21 መስማት የተሳናቸው ሴቶችን ጨምሮ 31 ሰራተኞች ቀጥሮ ያሰራል።

‘ተኪ’ እስካሁን ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ የወረቀት ቦርሳዎችን አምርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም