የክልሉ ኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች ውጤት እያመጡ ነው-አቶ ርስቱ ይርዳው

5

ቡታጅራ፤ ግንቦት 26/2014(ኢዜአ)፡ በደቡብ ክልል ኢንቨስትመንትን ለማበረታት የተከናወነው ተግባራት ባለሀብቶችን ከመሳብ አንጻር አጥጋቢ ውጤት ማስገኘታቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ርስቱ ይርዳው በቡታጅራ ከተማ የሚገኘውን ደስታ የአልባሳት ፋብካሪን  ከጎበኙ በኋላ እንዳሉት፤ መንግስት በአምራች ኢንደስትሪው መስክ ባለሀብቶችን በብዛት ለመሳብ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

የተሰራው ስራ ውጤት ማስገኘቱን ጠቁመው ‘ደስታ ሀላፊነቱ የተወሰነ  አልባሳት አምራች ኢንደስትሪ’ ቦታ በመረከብ ወደ ስራ በመግባቱ የሚታይ ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።

 ለአንድ ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል የፈጠረው የአልባሳት ፋብሪካው  ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።

የ’ደስታ ሀላፊነቱ የተወሰነ  አልባሳት አምራች ኢንደስትሪ’ ስራ አስኪያጅ አቶ እዮብ በቀለ በበኩላቸው፤  ስራውን ለማሳደግ የማስፋፊያ ግንባታ መጀመሩን ገልጸው  የሲሚንቶ  አጥረት እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል።

የሲሚንቶ እጥረት ችግሩ ከተፈታ የማስፋፊያ ግንባታውን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ወደ ስራ እንደሚገባና የሰራተኛውን ቁጥር ወደ አምስት ሺህ ለማሳደግ መታቀዱን ገልጸዋል።

የሲሚንቶ እጥረት ችግሩን ለመፍታት የክልሉ መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መነጋገሩን የጠቆሙት አቶ ርስቱ፤ለባለሀብቱ ጥያቄ  አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።