በህዋ ሳይንስና ስነፈለክ ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል ክፍተት ለመሙላት ያለመ የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ

3

ጎባ ግንቦት 26/2014 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጋር በህዋ ሳይንስና ስነፈለክ ዘርፍ ምርምሮችን በቅንጅት ለማካሄድና የሰለጠነ የሰው ኃይል ክፍተትን ለመሙላት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር የሺሩን አለማየሁና የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር በዛብህ ወንድሙ ናቸው፡፡

ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር የሺሩን አለማየሁ ከስምምነቱ በኋላ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ኢንስቲትዩቱ በአስትሮኖሚ (ስነፈለክ) እና ህዋ ሳይንስ ዘርፍ ላይ ጥናት በማካሄድ አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል፡፡

በተለይ በዘርፉ የሚታየውን የተማረ የሰው ኃይል ክፍተትን ለመሙላት ከአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ከመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተፈራረመው የመግባቢያ ሰነድ የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን የገለጹት ዶክተር የሺሩን፤ ስምምነቱ ምርምሮችን በቅንጅት ለማካሄድና በዘርፉ የሚስተዋሉ የሰው ኃይል እጥረትን ለማቃለል ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡

የስነ ፈለክና የህዋ ሳይንስ ጥናት ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት በምታደርገው ጥረት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ምክትል ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

በተለይ ባሌና አካባቢዋ የምትታወቅበትን የቱሪዝም መስህቦች መረጃን በማደረጀትና በማልማት ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆኑ ዕድል እንደሚፈጥርም አክለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በቱሪዝም፣ ተፈጥሮ ኃብት ጥበቃና በግብርና መስክ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እያደረገ የሚገኘውን ጥረት በማገዝ ረገድ ስምምነቱ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ያሉት ደግሞ የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር በዛብህ ወንድሙ ናቸው፡፡

የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ በተለይም የዘርፉ ምሁራን የተሻለ አቅምና እውቀት ካላቸው የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች ጋር ለመቀራረብና ትብብር ለመፍጠር ጭምር ዕገዛ እንደሚያደርግ አመልክተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ከዚህ በፊት ያደርጓቸው የነበሩ የንድፈ ሐሳብ ምርምሮች ወደ ተግባር የሚለውጡበት አሰራር እንዳልነበረ ዶክተር በዛብህ አመልክተዋል።

አሁን የተደረገው ስምምነት በዘርፉ የጋራ ምርምር ለማድረግ ተጨባጭ ትምህርትና ልምድ ለማግኘትና ምርምሮችን ለሃገር እድገት ለማዋል ተባብሮ ለመስራት እንደሚያስችልም ነው የገለጹት፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ ከተገኙ የዩኒቨርሲቲው መምህራን መካከል አቶ ሌንጮ ሳሙኤል እንዳሉት በዩኒቨርሲቲው ደረጃ ሲያደርጉ በነበሩ ምርምሮች በግብዓትነት የሚውሉ ሳይንሳዊና አካባቢያዊ መረጃዎችን ለማግኘት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

አሁን ዩኒቨርሲቲያቸው ከኢንስቲትዩቱ ጋር ያደረጉት ስምምት መረጃዎቹን በነጻ ለማግኘት ከመርዳቱም ባሻገር መረጃን ለማግኘት ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት እንደሚያስቀር ነው የተናገሩት፡፡

ከኢንስቲትዩቱ ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር ክህሎትና ዝንባሌ ላላቸው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና መምህራንም የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያገኙበት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው መምህር አቶ ሀሰን ሁሴን ናቸው፡፡

የስነ ፈለክና የህዋ ሳይንስ ጥናት ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት በሚታደርገው ጥረት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ይነገራል፡፡