አዲሱ ዓመት መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታትና አንድነትን ለማጠናከር ሁሉም ዜጎች በተባበረ ክንድ እንዲሰሩ ተጠየቀ

1561

አዲስ አበባ ጳጉሜ 4/2010 አዲሱ ዓመት መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታት በር የሚከፍቱና አንድነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎች ለማከናወን ሁሉም ዜጎች በተባበረ ክንድ እንዲሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ ዓመት በመረዳዳት፣ በመስጠት ከሚገኘው በረከትና ደስታ መቋደስ የሚቻልበት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን በገለጹበት መግለጫ፤ ኢትዮጵያውያን በመረዳዳትና በአንድነት በመቆም ተዓምር መስራት እንደሚችሉ በተግባር መታየቱን ጠቅሰዋል።

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአዛውንቶችና ጧሪ የሌላቸው አሮጊቶች የፈረሰ ቤታቸውን ለማደስ የተደረገውን እንቀሰቃሴ ለአብነት ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ኢትዮጵያውያን ስንተባበር ምን ማድረግ እንደምንችል በገሃድ ያሳየ ነው” ብለዋል።

በአዲሱ ዓመት ሁሉም ዜጎች እንዲተባበሩ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ ሁሉም ተጋግዞ መጪውን ዘመን በተስፋ መቀበል እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን የሚፈለገውን ሰላም ካረጋገጥን ያለውን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብትና ወጣት ሃይል በመጠቀም ጠንክሮ መስራት ከተቻለ እንደሌሎቹ ሀብታም አገሮች ሌሎችን መርዳት እንደሚቻል ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የራስን ችግር መፍታት የሚቻለው በራስ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በመጨረሻም አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር የአንድነት፣ የመደመርና የመዝለቅ እንዲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመኝተዋል ።