የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመንግሥታትን ግንኙነት በማጠናከር የመሰረተ-ልማት ፈተናዎችን እያቃለለ ነው

520

ግንቦት 25/2014( ኢዜአ) የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመንግሥታትን ግንኙነትና የሕዝቦችን አንድነት በማጠናከር የመሰረተ-ልማት ፈተናዎችን በማቃለል ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑ ተገለጸ።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ 38 ሚሊየን ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ የ7 ቢሊየን ብር የልማት ሥራ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መከናወኑም ተገልጿል።

አራተኛው የዓለም የበጎ ፈቃደኝነት የ2022 ዓመታዊ ሪፖርት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ “እኩል እና  አካታች ማኅበረሰብ መገንባት” በሚል መሪ ሀሳብ ይፋ ሆኗል።

ዓለም አቀፉ የበጎ ፈቃደኞች አገልግሎት በበጎ ፈቃደኞች እና በአፍሪካ መንግሥታት መካከል የትብብር መንፈስን በማሳደግ ልማትን ለማሳለጥ እንደሚያግዝ ተገልጿል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት አሸናፊነቱን ለማስቀጠልና ለበጎ ፈቃደኞች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከ21 ሚሊየን በላይ በጎ ፈቃደኞች 7 ቢሊየን ብር የሚገመት የልማት ሥራ በማከናወን ከ38 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የችግኝ ተከላና ደም ልገሳ፣ ትምህርት፣ የከተማ ጽዳት አገልግሎት፣ የግብርና ልማትና አረጋዊያንን መርዳት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የተሳተፉባቸው ዘርፎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሴኔጋል እና የአፍሪካ ሕብረት ቋሚ ተወካይ አምባሳደር መሀመድ ላሚን ቲያው፤ በአፍሪካ እየተካሄደ የሚገኘው የበጎ ፈቃደኞች ልማት በዜጎችና መንግሥታት መካከል ተባብሮ መሥራት ያስችላል ብለዋል።

በተለይም የአፍሪካ ችግሮችን በአፍሪካዊ መፍትሔ እልባት ለማበጀት የበጎ ፈቃደኞች አገልግሎት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

በመንግሥታቱ ድርጅት የደቡብ አፍሪካ ቀጣና የበጎ ፈቃደኞች ኃላፊ ሉሲ ነዱንጉ፤ የመንግሥት አካላትና በጎ ፈቃደኞች ትብብር አፍሪካ በ2063 ለማሳካት ያስቀመጠችውን የልማት ግብ እውን ለማድረግ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ከሌሎች ክፍለ አህጉራት አንጻር ሲታይም የአፍሪካ በጎ ፈቃደኞች አገልግሎት የልማት ሥራ እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል።

የዘንድሮው የዓለም የበጎ ፈቃደኝነት ሪፖርት ግኝት ለዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ውይይቶች፣ በአፍሪካ ላሉ ባለድርሻ አካላት፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና ተቋማት ተጨማሪ ግብዓት ይሆናል ተብሏል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ በኢትዮጵያ ያሉ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (የተመድ) የሥራ ኃላፊዎች፣ በጎ ፈቃደኛ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንዲሁም ሌሎች አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም