የጅማ ዩኒቨርሲቲው ለአብርሆት ቤተ መጽሀፍት የተለያዩ መጻህፍትን ለሁለተኛ ጊዜ አበረከተ

146

ጅማ፤ ግንቦት 25/2014 (ኢዜአ)፡-ጅማ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዙር የመፅሀፍት ድጋፍ አሰባሰብ ከ900 በላይ መፅሐፍትን ለአብርሆት ቤተ-መፅሐፍት አበረከተ። 

የጅማ ዩኒቨርሲቲ አብያተ-መፅሐፍት ዳይሬክቶሬት ወይዘሮ አዲስዓለም ጉልማ  እንደገለጹት ዩኒቨርስቲው በመጀመሪያው ዙር የመፅሀፍት ድጋፍ አሰባሰብ መርሐ ግብር ከ3 ሺህ በላይ መፅሐፍትን ለአብርሆት ቤተ-መፅሐፍት መለገሱን አስታውሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው በሁለተኛው ዙር ያበረከታቸው መጽሀፍት ስፖርት፣ ቢዝነስ፣ ጤና፣ ማህበራዊ ሳይንስን ጨምሮ  94 የተለያዩ ርእሰ ጉዳዮችን ያካተቱ 900  መጽሀፍት መሆናቸውን ተናግረዋል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚደንት ዶክተር ታደሰ ሀብታሙ በበኩላቸው ተቋሙ ለበርካታ አመታት ያካበታቸው እውቀቶች በአብያተ-መፅሐፍቱ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ''እነዚህን መጽሀፍት ዜጎች ሊያገኟቸው የሚችሉበት አንዱ መንገድ እንደ አብርሆት ያለ  ቤተ-መፅሐፍት በመሆኑ መጽሀፍቱን መደገፍ አስፈልጓል'' ብለዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ "ኢትዮጵያ ታንብብ" በሚል ተነሳሽነት የትውልዱን እውቀት፣ ክህሎትና ስብዕና ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም