12ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ተከፈተ

2

ግንቦት 25/2014( ኢዜአ) 12ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትና ባዛር በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽንና ገበያ ልማት ማዕከል ተከፈተ፡፡

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ የንግድ ትርዒትና ባዛር ነው፡፡

በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽንና ገበያ ልማት ማዕከል ከግንቦት 25 ቀን 2014 ዓ. ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት “የኢትዮጵያን ይግዙ፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ!” በሚል መሪ ሀሳብ ይካሄዳል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ፤ በዚህ ወቅት እንዳሉት ለአገር ብልጽግና የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ቅንጅት አስፈላጊ ነው፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ  የኢንቨስትመንት መስክ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች  ከመንግሥት የተሟላ ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

መንግሥት ባለሃብቱን በመደገፍና የግሉን ዘርፍ በማጠናከር አገራዊ የኢኮኖሚ ዘርፉን የማሳደግ ከፍተኛ ፍላጎትና ቁርጠኝነት እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን፤  የኢትዮጵያን ጥቅል ኢኮኖሚ ለማሳደግ ከግሉ ዘርፍ ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በንግድ ትርኢትና ባዛሩ ከ60 በላይ ኢንተርፕራይዞች የተሳተፉ ሲሆን፤ ከዓለም አቀፍ ንግድ ተቋማት ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ያግዛቸዋልም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው፤ በመርሃ-ግብሩ ከ250 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች፣ የንግድ ተቋማት፣ ኢንተርፕራይዞችና ነጋዴዎች ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡

ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የንግድ ተቋማት፣ ኢንተርፕራይዞች፣ እንዲሁም ካምፓኒዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ያስተዋውቁበታልም  ብለዋል፡፡