ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጫናዎችንና አገራዊ ፈተናዎችን ተቋቁማ በዘላቂ የልማት ግቦች ላይ የተሻለ አፈጻጸም አሳይታለች

ግንቦት 25/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጫናዎችንና አገራዊ ፈተናዎችን ተቋቁማ በዘላቂ የልማት ግቦች ላይ የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቷን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር በቀጣይ ሐምሌ ወር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ ሪፖርት ፎረም ላይ የሚያቀርበውን ያለፉት ስድስት ዓመታት የዘላቂ ልማት ግብ አፈጻጸም ሪፖርት በተለያዩ አካላት እያስገመገመ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በሐምሌ ወር ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የዘላቂ ልማት ግቦች አፈጻጸም ሪፖርት የምታቀርብ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ ገልጸዋል።

በጥልቅ መረጃ ላይ ተመስርቶ በቀረበው የዘላቂ ልማት ግቦች አፈጻጸም ሪፖርት መሰረት ኢትዮጵያ እቅዱን ማሳካት የሚችል ሥርዓት መገንባቷን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ 62 በመቶ የሚሆነው በጀት ለድህነት ተኮር ተቋማት ስለሚመደብ በ1999 ዓ.ም ከነበረው የድህነት ምጣኔ በግማሽ መቀነስ ተችሏልም ብለዋል፡፡

"የሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችና ፈተናዎችን በመቋቋም ድህነትን ማስወገድና ረሀብን ማጥፋት በሚለው የዘላቂ ልማት ግቦች ላይ ስኬታማ ነበረችም " ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ድርቅ፣ ጦርነት፣ የአንበጣ መንጋ፣ ጎርፍ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝና ሌሎች ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ፈተናዎችን ተቋቁማ ውጤት ማስመዝገቧንም ጠቅሰዋል።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሕብረተሰቡ ተሳትፎ፣ የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴዎች ለዓለም ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉም አብራርተዋል። 

ከዘላቂ የልማት ግቦች መካከል የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ዛሬም ያልተሻገረችው ፈተና ስለሆነ በቀጣይ በትኩረት መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

በተመባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚቀርበውን በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ሪፖርት የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት የምንጠቀምበት ይሆናልም ነው ያሉት።

ለኢትዮጵያ የተዛባ እይታ ያላቸውና በማህበራዊ ድረ-ገፆች በሐሰተኛ መረጃ ሕዝብን የሚያደናግሩ አካላትን ለማጋለጥ እንጠቀምበታለንም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም