የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ እውቅናና ሽልማት አበረከተች

155
አዲስ አበባ ጳጉሜ 4/2010 ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሃላፊነት በመጡ በአጭር ጊዜያት ውስጥ ለቤተክርስቲያን አንድነትና ለአገር ሰላም  በሰሩት ጉልህ ስራ አውቅናና ሽልማት ተበረከተላቸው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር በሚል ስያሜ ለሁለት የተከፈሉ የሲኖዶስ አባላቶቿ ወደ አንድ እንዲመጡ በተደረገው እርቀ ሰላም ላይ የጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሚና የጎላ እንደነበር በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል። የሲኖዶሱ ወደ አንድ መምጣትን ተከትሎም ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ ኑሯቸውን በአሜሪካ ያደረጉት ብጹዕ ወ ቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ እና ሌሎች ቅዱሳን አባቶች ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ብጹዕ ወ ቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቀነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሳት ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘ መንበረ ተክለሃይማኖት በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤  አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ እንዲኖር ጠቅላይ ሚንስትሩ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ዳግም አንዲገናኙና ጠቡ ተወግዶ የአንድነት አስተሳሰብ እንዲሰርጽ  ጠቅላይ ሚንስትሩ ትልቅ ስራ መስራታቸውንም አክለዋል። ዜጎች የሰላም ዋስትና አንዲያገኙ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቀን ከሌት እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ብጹዕነታቸው፤ ለእነዚህና ሌሎች በጠቅላይ ሚንስትሩ የተመዘገቡ ለውጦችን ለመደገፍ  የእውቅና ሽልማቱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። "አጅግ አስቸጋሪ ሆኖ የሚታየው የሰው ልጆች ህይወት የሰላም ዋስትና እጦት ስለሆነ ዋስትና እንዲኖር ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያለ አንዳች እረፍት ሌትና ቀን እየተንቀሳቀሱ የተበታተነውን በማሰባሰብ የጠፋውን በማፈላለግ የተራራቀውን በማቀራረብ የተጣላውን በማስታረቅ የሚሰሩት ስራ በእጅጉ የሚደነቅ ነው። ስለሆነም ለሀገርና ለወገን እንዲሁም ለቤተክርስቲያን ስለፈጸሟቸው እና ስለሚፈጽሟቸው አበይት ተግባራት ድጋፋችንንና ምስጋናችንን ለመግለጽ ያህል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናችን ትንሽ ሽልማት አዘጋጅታለች።” ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው ሽልማቱ ለለውጥ የበለጠ እንዲተጉ አንደሚያነሳሳቸው ገልጸው፤ "ስሰራ ክብርና ሽልማት እንዳለ ሁሉ ሳጠፋ ወቀሳና ቅጣት እንደሚኖር ተገንዝቤያለሁ" ብለዋል። ኢትዮጵያ ያሰበችው ለውጥ እውን እንዲሆን ቤተክርስቲያኒቱ የማይተካ ሚናዋን መወጣት እንዳለባትም አስገንዝበዋል። "ይህቺ ታላቅ ቤተክርስቲያን ያሏትን መንፈሳዊ ፣ ባህላዊና ታሪካዊ መዋቅራዊ አቅሞችን በመጠቀም ሀገራችን የጀመረችው ለውጥ ከታሰበለት ግብ እንዲደርስና ሁላችንንም ተጠቃሚ አንዲያደርግ  በማንም የማይተካ ሚናዋን መወጣት አለባት። መልካም አስተዳደር አንዲሰፍን ሙስና እንዲጠፋ ሌብነት ነውር ስለመሆኑ አርስበርስ መለያያትና መጠፋፋት ከታሪካችን መድረክ እንዲፋቅ ጥላቻና መለያየት እንዲወገድ ለአገልጋዮቿ ሁሉ ተልዕኮ ሰጥታ በማሰማራት በስፋት እንደምታስተምር ጥርጥር የለኝም።” ቤተክርስቲያኒቱ እውቅናና ክብር ስትሰጥ የሰራነው ስራ በቂ ነው ብላ እንደማይሆን አምናለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚነስትሩ፤ እንደ ቤተክርስቲያኒቱ ያሉ ታላላቅ ተቋማት የጀመሩትን ጉዞ ካበረታቱትና ከደገፉ  ካሰቡት ቦታ መድረስ እንደሚችሉ ተናግረዋል። "የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ይህንን እወቅናና ክብር ስትሰጥ የሰራነው በቂ ነው ብላ እንደማይሆን አምናለሁ። ነገር ግን የጀመርነው የፍቅር የእርቅና የመደመር ጉዞ ከመጠፋፋትና ከመተላለቅ ከጥላቻና ከመከፋፈል በእጅጉ የላቀና ወደምንፈልገው የስልጣኔ ምዕራፍ ያደርሰናል ብላ በማመኗ እንደሆነ እተማመናለሁ። እንደ እርሷ ያሉ ታላላቅ ተቋማት ይህንን ጉዞ ካበረታቱትና  የሚጠበቅባቸውን በጽናትና ትጋት ከተወጡ ካሰብነው ቦታ በቶሎ መድረሳችን የማይቀር ነው።”    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም