ፈረንሳይ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሪፎርም ትደግፋለች – የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ

3

ግንቦት 25/2014 (ኢዜአ) ፈረንሳይ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የኢኮኖሚ ሪፎርም ትደግፋለች ሲሉ የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ የአፍሪካ ዳይሬክተር ክርስቲያን ዮካ ተናገሩ።

ዳይሬክተሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሁለቱ አገራት ግንኙነት 125 ዓመታት ማስቆጠሩን አስታውሰው በነዚህ ዓመታት የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ጠንካራ ትስስር ተፈጥሯል ብለዋል።  

ኢትዮጵያ ቅድሚያ የሰጠቻቸው አገራዊ የልማት አጀንዳዎች እንዲሳኩ ፈረንሳይ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ነው የገለጹት።

የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ ላለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው ቀደም ባሉት ዓመታት በተወሰኑ የልማት ስራዎች ላይ ይሳተፍ ነበር ብለዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ተሳትፎውን በማስፋት ትልልቅ የልማት ስራዎችን በመስራት የኢትዮጵያ አጋር መሆኑን እያሳየ ይገኛል ብለዋል።      

የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ የአፍሪካ ዳይሬክተር ክርስቲያን ዮካ የኢትዮጵያ መንግስት እያካሄደ ያለውን የኢኮኖሚ ሪፎርም ፈረንሳይ እንደምትደፍም ገልጸዋል። 

በቀጣይ ትኩረት የሚሰጣቸው ዋና ዋና ጉዳዮችን በተመለከተ ከኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለግብርናው፣ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ እንዲሁም ለስራ እድል ፈጠራ  ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን መረዳታቸውን ገልጸዋል።   

ኢትዮጵያ ተለዋዋጭ የከተሜነት ሂደት እያጋጠማት መሆኑን የሚናገሩት ክርስቲያን ዮካ ከተሞች የተመጣጠነ ልማት እያገኙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

በሚቀጥሉት አመታት መንግስት የያዛቸውን የልማት ውጥኖች ለማሳካት በተለያዩ ዘርፎች ላይ በትኩረት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።