የኢትዮጵያ ስጦታዎች ዓለም አቀፍ ፌስቲቫል ተጀመረ

117

ግንቦት 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅ ያለመ ‘የኢትዮጵያ ስጦታዎች’ ዓለም አቀፍ ፌስቲቫል ተጀመረ።

ፌስቲቫሉ ከአንድ ወር በኋላ በሰሜን አሜሪካ፣ እስያ፣ አውሮፓና በመካከለኛው ምስራቅ በሚገኙ አገራት እንደሚዞር ተገልጿል።

‘የኢትዮጵያ ስጦታዎች’ ዓለም አቀፍ ፌስቲቫል ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ የማህበረሰብ ክፍሎችና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት በወዳጅነት አደባባይ እየተካሄደ ነው።

ዝግጅቱ የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ ለዓለም በማስተዋወቅና የተዛቡ ትርክቶችን በማረም የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመጨመር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንዳሉት፤ ፌስቲቫሉ ኢትዮጵያ ያላትን ባህል በማስተዋወቅ ፋይዳው የጎላና በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ለመላው ዓለም በማሳየት የገጽታ ግንባታ እንዲሁም ኢንቨስትመንት ለመሳብ ያግዛል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ምድረ-ቀደምት መሆኗን ተናግረዋል።

ይህንን ሀብት ወደ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለመቀየር የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ገልጸዋል።

በፌስቲቫሉ መክፈቻ ማስጀመሪያ የጥበብ፣ ግብርና፣ ዕደ ጥበብ፣ የቡና አፈላልና ሌሎች ትዕይንቶች ለእይታ ቀርበዋል።

ፌስቲቫሉ ከአንድ ወር በኋላ በጀርመን፣ አሜሪካ፣ ካናዳና በተለያዩ የዓለም አገሮች በመዘዋወር ኢትዮጵያ ያላትን ባህል በማስተዋወቅ የገጽታ ግንባታ እንደሚከናወን  ተገልጿል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም