ለምክር ቤት አባላት የተሰጠው ሥልጠና አዲስ እይታን በመፍጠር የማስፈጸም አቅማቸውን የሚያጎለብት መሆኑ ተገለጸ

211

ግንቦት 25/2014 (ኢዜአ) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አዲስ እይታን በመፍጠር የወከሉትን ሕዝብ የሚጠቅም ሀሳብ ማፍለቅ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ሥልጠና ማግኘታቸውን የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ሥልጠና የአባላቱን እይታ በማስፋት የምክር ቤቱን የማስፈጸም አቅም ያጎለብታልም ተብሏል።

"አዲስ ፖለቲካዊ እይታ! አዲስ ሀገራዊ እመርታ!" በሚል መሪ ሀሳብ ለብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተጠናቋል፡፡

የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ፤ የአቅም ግንባታ ሥልጠናው በአዲሱ እይታ ላይ ግልጽነትን የሚፈጥርና ከታሰበው ግብ ለመድረስ መሸጋገሪያ ድልድይ ነው ብለዋል፡፡

ከለውጡ በኋላ የሰብዓዊ መብት፣ የፋይናንስና የፍርድ ቤት ሕጎችን እንዲሁም ሌሎች አፋኝ ሕጎችን ማሻሻል ቢቻልም ለዘመናት ተሰርቶ የጎመራው የጥላቻ ትርክት ለውጡን በሚፈለገው ልክ እንዳይራመድ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት በችግር ውስጥም ሆኖ የተሻለ ምርጫ በማድረግ ብልጽግና ፓርቲ መንግሥት መስርቶ ጉባኤ አካሂዶ አዲስ የለውጥ መንገድ ጀምሯል ብለዋል፡፡

የተጀመረውን የለውጥ መንገድና አዲስ እይታ እውን ለማድረግ ደግሞ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትንና በየደረጃው ያሉ አመራር አካላት ሥልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

የሥልጠናው መሰረታዊ ዓላማም በዚህ አዲሱ እይታ ላይ ግልጽነት በመፍጠር የተሻለ የክትትል፣ ድጋፍና የማስፈጸም አቅም መገንባት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ተዘርቶ የበቀለው የቂምና ጥላቻ ትርክት በአንድነት በወንድማማችነትና እህትማማችነት ትርክት ለመቀየር የጋራ መግባባት ላይ መድረስ አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በመሆኑም የምክር ቤቱ አባላት ሥራዎቻቸውን ሲያከናውኑ ኢትዮጵያዊ አንድነትንና መተሳሰብን ማዕከል አድርገው መምራት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

በአዲሱ እይታ ለኢትዮጵያ ፈተና ለሆነው የሰላም ደህንነትና ጸጥታ፣ ለአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ለግብርና ምርታማነት፣ ለፈጣንና ቀልጣፋ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ እና ለሥራ እድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት ይሰጣል ብለዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ የመንግሥታዊ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ በሕብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ ጥያቄ የሚቀርብበት መሆኑን አንስተዋል፡፡

በመሆኑም የመንግሥት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል ለሕዝቡ ቅሬታ ምላሽ ለመስጠት የምክር ቤት አባላት አቅም ማደግና አንድ አይነት አገራዊ እይታ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የአቅም ግንባታ ሥልጠናውም የአገልግሎት አሰጣጡንና የፋይናንስ ሥርዓቱን በመቆጣጠር ዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲን ለመገንባት እንሰራለን ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት ፕሮጀክቶችን ከተለመደው የማጓተትና ከጥራት በታች የመሥራት መጥፎ አባዜ አስወጥቶ እንደ ምሳሌ የሚሆን አፈጻጸም ተመዝግቧል ብለዋል፡፡

የግብርና፣ ኢንዱስትሪና ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ከዜጎች የመልማት ጥያቄ ጋር ትይዩ መሄድ ይችል ዘንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተሰጣቸውን የመንግሥትን አስፈጻሚ አካላትን የመቆጣጠር ሥልጣን ገቢራዊ ሊያደርጉት ይገባል ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ እንደ መንግሥትና መሪ ድርጅት የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለውጥ ማምጣት የሚችል የአቅም ግንባታ እንዲወስዱ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም