ዩኒቨርሲቲው ለፖሊስ ተቋማት የለውጥ ስራዎች ውጤታማነት በጥናትና ምርምር የተደገፉ ተግባራትን እያከናወነ ነው

85

ግንቦት 25/2014 (ኢዜአ) ለፖሊስ ተቋማት የለውጥ ስራዎች ውጤታማነት በጥናትና ምርምር የተደገፉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ 4ኛውን አገራዊ ፖሊስ ጥናት ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው።   

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መስፍን አበበ፤ በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ባስተላለፉት መልእክት ለፖሊስ ተቋማት የለውጥ ስራዎች ውጤታማነት በጥናትና ምርምር የተደገፉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የፖሊስ የለውጥ ሥራዎች እንዲሳኩ ዩኒቨርሲቲው በትምህርት፣ ሥልጠና እና በጥናትና ምርምር ዘርፍ የተጠናከረ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑንም አብራርተዋል።

ለተለያዩ ፖሊስ ተቋማት ሥርዓተ-ትምህርት በመቅረጽ የተሻለ ሥልጠና እና ትምህርት ተደራሽ እንዲያደርጉ የበኩሉን ሲወጣ መቆየቱንም አስታውሰዋል።   

በክልሎችም የፖሊስ ተቋማት ጠንካራ ሥራ እንዲሰሩ በጥናትና ምርምር የማገዝ ሥራ እያካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህ በፊት የተካሄዱ የጥናት ሲምፖዚየሞች ለፖሊስ ሥራዎች መጠናከር አስተዋጽኦ ያበረከቱ የጥናት ውጤቶች መቅረባቸውን አስታውሰው፤ ተግባራዊ እንዲሆኑ የበለጠ መሥራት ይገባል ብለዋል።     

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ዶክተር ደመቀ አጪሶ፤ በኢትዮጵያ የሚታሰበው እድገት እንዲመጣ ከተፈለገ ውስጣዊ ሰላምን ማረጋገጥ የግድ ይላል ብለዋል።  

ለዚህ ደግሞ የፖሊስ ተቋማት አደረጃጀት መጠናከርና ዘመናዊ አሰራርን መከተል ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በጸጥታ አካል ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ የሁሉም አካላት ትብብር አስፈላጊ ስለመሆኑም ተናግረዋል።   

የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሕብረተሰቡም ተሳትፎውን ሊያጠናክር እንደሚገባም ዶክተር ደመቀ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የሚፈጸሙ ወንጀሎች ከሕብረተሰቡ የሚሸሸጉ ባለመሆናቸው ፖሊስ ከሕብረተሰቡ ጋር ያለውን የትብብር ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር መስራት አለበት ብለዋል።    

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ጥናትና ምርምር ኃላፊ ዶክተር ሲሳይ ዘለቀ፤ የፌደራል ፖሊስ የጀመራቸው የለውጥ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ዩኒቨርሲቲው የድርሻውን በመወጣት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።   

ሲምፖዚየሙ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን 17 ያህል የጥናት ውጤቶች እንደሚቀርቡም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም