ኢትዮ ቴሌኮም በ66 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የዲጂታል መማሪያ ማዕከላት አቋቋመ

466

ግንቦት 25/2014 (ኢዜአ)፡ኢትዮ ቴሌኮም በአገር አቀፍ ደረጃ በ66 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የዲጂታል መማሪያ ማዕከላትን አቋቋመ።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ በአዲስ አበባ ከፍተኛ 23 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው የማዕከላቱን ሥራ መጀመር ይፋ አድርገዋል።

ኩባንያው በኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚን ዕውን ለማድረግና አገር ተረካቢ ዜጎችን በዕውቀት ለማነጽ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮ ቴሌኮም በአገር አቀፍ ደረጃ በ66 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የዲጂታል መማሪያ ማዕከላትን መሰረተ-ልማት ማሟላቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።

በፕሮጀክቱም የትምህርት ቤት መገልገያ መሳሪያዎችን ዘመናዊ ማድረግ እና ከፍተኛ ፍጥነት ያለው መደበኛ የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት ይቻላል ብለዋል።

በትምህርት ገበታቸው ተማሪዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂን እንዲያውቁ ለማስቻልም ጉልህ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አንስተዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ከተቋቋሙት ማዕከላት 18ቱ በአዲስ አበባ ሲሆኑ ቀሪዎቹ በክልሎች መሆኑ ታውቋል።

የዲጂታል መማሪያ በማዕከላቱ ለ140 ሺህ 596 ተማሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፤ በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ለሚሆኑት ትምህርት ቤቶች ሥልጠና ይሰጣል ብሏል።

ማዕከሉ ከተከፈተባቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ የከፍተኛ 23 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በበኩላቸው፤ የማዕከሉ መከፈት የበለጠ የዲጂታል ቴክኖሎጂን ለመጠቀም እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።

በትምህርት ቤቱ ከዚህ በፊት የኮምፒውተርና የኢንተርኔት አገልግሎት ቢኖርም በሚፈልጉት መልኩ አገልግሎት ሳያገኙ መቆየታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው ተማሪዎች ገልጸዋል።

የማዕከሉ መቋቋም በቀጣይ የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው በመሆኑ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ገመቹ በከሬ፤ የማዕከሉ መከፈት ተማሪዎች ከቴክኖሎጂው ጋር የበለጠ እንዲተዋወቁና ውጤታማ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም