ባህላዊ እሴቶች ለሀገር አንድነትና ሰላም የሚያበርክቱትን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ይሰራል – ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

4

ሚዛን አማን፤ ግንቦት 25/2014 (ኢዜአ)፡ ባህላዊ እሴቶች ለሀገር አንድነትና ሰላም የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናገሩ።

በክልሉ የመጀመሪያ የሆነው የባህል ፌስቲቫልና ኤግዚቢሽን “ባህላችን ለዘላቂ ሰላማችንና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ቃል ዛሬ በቦንጋ ተከፍቷል።

በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ኢትዮጵያዊ የባህል እሴቶች ለሀገር አንድነትና ሰላም ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው።

ክልሉ ያልተበረዙ በርካታ ባህሎች ያሉት መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይ የእርቀ ሰላምና ዳኝነት ወጎችና ሥርዓቶች ለሀገር ግንባታ ያላቸውን  ድርሻ ለማሳደግ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

”ከአባቶቻችን የተቀበልናቸውን ጠቃሚና ውብ ባህላዊ እሴቶቻችንን የምናለማበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፣  ፌስቲቫሉም መልካም የሆኑ ባህሎች ለሀገር አንድነትና ሰላም ያላቸውን ድርሻ የምናንጸባርቅበት ነው” ብለዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልማሃዲ በበኩላቸው ባህል ሀገራዊ ገፅታን የሚገነባ የኢትዮጵያውያን እሴት መሆኑን ተናግረዋል።

ባህል የህብረተሰብ ስብዕናን በመጠበቅና ሥነ ምግባር ከማላበስ አንጻር አቅም አለው ብለዋል።

በተለይ የዕደ ጥበብ ውጤት የሆኑ ባህላዊ ቁሳቁስን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ያመላከቱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ተቋማቸው ዘርፉን ለማሳደግ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፍ አስታውቀዋል።

 የባህል ፌስቲቫልና ኤግዚቢሽኑ በክልሉ የሚገኙ 13 ብሔረሰቦችን በማስተዋወቅ አንድነትን ለማጠናከር ታስቦ መዘጋጀቱን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ ናቸው።

በዝግጅቱ ባህላዊ አልባሳት፣ ምግብና መጠጦች፣ እንዲሁም የዕደ ጥበብ ቁሳቁሶች መቅረባቸውን ተናግረዋል።

የባህል ፌስቲቫልና አውድ ርዕዩ እስከ ግንቦት 27/2014 ዓ.ም  ድረስ እንደሚቆይ የወጣው መርሐ ግብር ያመለክታል።

በዝግጅቱ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የክልሉን መንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞን ጨምሮ  የፌዴራል፣ የክልልና የየዞኖች የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የባህል ቡድኖች ተሳትፈዋል።