በባንኮች የደንበኞች የቁጠባ ሂሳብ መጠን 1 ነጥብ 6 ትሪሊየን ብር ደርሷል

167

ግንቦት 25/2014( ኢዜአ) በባንኮች የደንበኞች የቁጠባ ሂሳብ መጠን 1 ነጥብ 6 ትሪሊየን ብር መድረሱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሱፐርቪዥን ዳሬክተር ፍሬዘር አያሌው፤ የዜጎች የቁጠባ ባህል በሚፈለገው ደረጃ ላይ ደርሷል ባይባልም በእጅጉ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።

እስከ መጋቢት 2014 ዓ.ም ድረስ በባንኮች የደንበኞች የቁጠባ ሂሳብ መጠን 1 ነጥብ 6 ትሪሊየን ብር መድረሱን ተናግረዋል።

አጠቃላይ ባንኮች የሰጡት የብድር መጠን 1 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር ሲሆን የተበዳሪዎች ቁጥርም ከ350 ሺህ ማለፉን ገልጸዋል።

የባንኮች የቅርንጫፍ ብዛት፣ የሚሰጡት የብድርና ቁጠባ አገልግሎት፣ የተለያዩ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ለመስጠት ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ማዋል ለባንኮች ተደራሽነት መጨመር ምክንያት ስለመሆናቸውም ጠቅሰዋል።

ከቁጠባ ተደራሽነት አንጻር የተሻለ ቢሆንም የብድር ተደራሽነቱ ግን በአብዛኛው ለትልልቅ ተበዳሪዎች የተሰጠ በመሆኑ ውስንነት ያለበት መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይም በእርሻና ጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ እንዲሁም አነስተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰጠው ብድር ዝቅተኛ በመሆኑ በቀጣይ ትኩረት ይሻል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና ንግድ ባንክ  በመንግስት ቅድሚያ የተሰጣቸውን ዘርፎች በመደገፍ እየሰሩ እንደሚገኙም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

የግል ባንኮችም ቢሆኑ ግን በአገሪቱ የሚገኙ የልማት እንቅስቃሴዎችን እየደገፉ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

በግል ባንኮች በቂ የገንዘብ ክምችት አለመኖርና የብድር ስጋት መጨመር ለብድር ተደራሽነት ዝቅተኛ መሆን በምክንያትነት ተቀምጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም