በላስታ ወረዳ ለአሸባሪው ህወሃት ከ800 ሺህ ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ ሊያስተላልፉ የሞከሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

6

ግንቦት 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሰሜን ወሎ ዞን ላስታ ወረዳ ለአሸባሪው ህወሃት ከ800 ሺህ ብር በላይ የሆነ ጥሬ ገንዘብ ሊያደርሱ የነበሩ 11 ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የወረዳው ፖሊስ አስታወቀ።

የወረዳው ፖሊስ ፅህፈት ቤት ሃላፊ ኮማንደር ተገኘ ወርቁ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በህገ ወጥ መንገድ ለአሸባሪው ህወሃት ጥሬ ገንዘብ ለማስተላለፍ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመግታት ክትትል እየተደረገ ነው።

ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ባደረገው ክትትል ባለፉት ሶስት ቀናት ለአሸባሪው ቡድን ሊተላለፍ የነበረ 804 ሺህ 260 ብር ከነተጠርጣሪ አዘዋዋሪዎቹ ጋር በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ገልፀዋል።

ከተያዘው ጥሬ ገንዘብ ውስጥ 594 ሺህ 260 ብር ያህሉ ትናንት ሌሊት በባጃጅና በባለ አንድ ጋቢና ቶዮታ መኪና በኬሻ ተሸፍኖ ሊያልፍ ሲል በፀጥታ ሃይሉ በቁጥጥር ስር መዋሉን ኮማንደር ተገኘ ጠቁመዋል።

በህገ ወጥ መልኩ ለሽብር ቡድኑ ጥሬ ገንዘቡን ለማስተላለፍ በመሞከር ወንጀል የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦችና አንድ ባጃጅ በህግ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የህገ ወጥ ንግድንና የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ህብረሰተሰቡ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልና በወረዳው የሌሊት ጉዞ የተከለከለ መሆኑን በመገንዘብ አካባቢያቸውን በንቃት እንዲጠብቁ ኮማንደር ተገኘ ጥሪ አቅርበዋል።