መገናኛ ብዙሃን ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃን ለህዝቡ በማድረስ አፍራሽ መልዕክቶችን ማምከን ይችላሉ - የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

155

ደሴ ግንቦት 25/2014(ኢዜአ) መገናኛ ብዙሃን ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃን ፈጥነው ለህዝብ በማድረስ በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ አፍራሽ መልዕክቶችን ማምከን ይገባቸዋል ሲሉ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ምሁራን ገለጹ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር አቶ እንግዳወርቅ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት ህብረተሰቡን ወዳልተገባ ብጥብጥና ሁከት የሚያመሩ አፍራሽና አደገኛ መልዕክቶች በማህበራዊ ሚድያ በብዛት ይተላለፋሉ፡፡

አብዛኞቹ መልዕክቶች በብዛት የሚሰራጩት ደግሞ ትንሽ እውነትና ጫፍ ይዘው መሆኑን ጠቁመው፤ የመገናኛ ብዙሃን ወቅታዊና ትክክለኛውን መረጃ ቀድመው ለህዝብ በማድረስ እነዚህን አደገኛ መልዕክቶች ማምከን ይጠበቅባቸዋል፡፡

ጋዜጠኞችም ነጻነታቸውን ከሀገራዊ ኃላፊነት ጋር አዛምደው ሚዛናዊ ዘገባ መስራት እንጂ ነጻነት ስላላቸው ብቻ ሀገርንና ህዝብን አደጋ ላይ የሚጥል ሆኖ ከተገኘ መዘገብ የለባቸውም ብለዋል፡፡

አመራሩና የሚመለከተው አካልም አፍራሽ መረጃዎች በማህበራዊ ሚድያ እየተሰራጩ ህብረተሰቡን ከማደናገራቸው በፊት ሁነቶችን ቀድመው ለብዙሃን መገናኛዎች ማሳወቅና መረጃ መስጠት አለባቸው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

በማህበራዊ ሚድያ ውሸት እያራገቡ ብጥብጥና ሁከት ለማስነሳት፣ ሀገር ለማፍረስ የሚሰሩ "የጥፋት ኃይሎችን መንግስት በጥናት እየለየ ለሌሎች አስተማሪ የሆነ እርምጃ በመውሰድ ግዴታውን መወጣት" እንደሚገባም ተናግረዋል አቶ እንግዳወርቅ፡፡

መገናኛ ብዙሃን ዘወትር "ለሰላም፣ ለአንድነትና ለልማት ግንባር ቀደም ሆነው መስራት ይጠበቅባቸዋል" ያሉት ደግሞ ሌላው የዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር አቶ ኢብራሂም ሰይድ ናቸው።

ችግሮች ሲፈጠሩ እሳት ለማጥፋት ከመሯሯጥ  ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት ቀድሞ ህብረተሰቡን፣ ምሁራንና የሌሎችንም ሃሳብ ባካተተ መልኩ አተኩረው ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን በማህበራዊ ሚድያ የሚናፈሱ አፍራሽ መልዕክቶችን በመመከት ለህብረተሰቡ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ የማድረስ ሀገራዊ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

ብዙሃን መገናኛዎች በሚሰሩት ዘገባ ህብረተሰቡ እንደሚጠቀም ሁሉ ሲሳሳቱም የችግሩ ሰለባ ስለሚሆን ሙያዊ ስነ ምግባራቸውን ጠብቀው በጥንቃቄ ለሀገርና ለህዝብ የሚመጥን ዘገባ በወቅቱ ማድረስ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

በመሆኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን አደገኛ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እንዲስተካከል ሁሉም መረባረብ እንዳለበትም ነው አቶ ኢብራሂም ያሳሰቡት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም