የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር የአገሪቷን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት መፍትሔ የሚሆን ነው

125


ግንቦት 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር የአገሪቷን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት ጥሩ የመፍትሔ አማራጭ መሆኑን በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አወር ገለጹ።

በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ጥያቄ ከቀረበላት ጀርመን አገራዊ የምክክር ሂደቱን ለመደገፍ ዝግጁ ናት ሲሉም አረጋግጠዋል።


አምባሳደር ስቴፋን አወር በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤በኢትዮጵያ የሚስተዋሉትን ውስጣዊ ችግሮች በመፍታት መፍትሔ ለማበጀት በጋራ መምከር ያስፈልጋል።


ኢትዮጵያ የምታካሂደው አገራዊ ምክክር ሁሉንም አሳታፊና አካታች ሆኖ ሲካሄድ ልዩነቶችን በመነጋገርና በመፍታት በቀላሉ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ያስችላል ብለዋል።


በአገራዊ ምክክሩ ለጋራ ችግሮች መንስኤ የሆኑ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? የሚለውን ቁልፍ ጥያቄ በማንሳትና በግልጽ መነጋገር የጋራ መፍትሔ ማምጣት ይቻላል ነው ያሉት።


የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር ሂደቱን ሁሉን አቀፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም አምባሳደር ስቴፋን አድንቀዋል።


የፌደራል ሥርዓት የምትከተለው ጀርመን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ ከቀረበላት የምክክር ሂደቱን በሚቻለው አቅም ሁሉ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።


የኢትዮጵያና ጀርመን የሁለትዮሽ ግንኙነት በጠንካራ ወዳጅነት የቀጠለ መሆኑን ጠቅሰው፤ "ኢትዮጵያ የጀርመን ስትራቴጂካዊ አጋራችን ናት" ሲሉ ተናግረዋል።


በልማት ድጋፍና ትብብር ጀርመን የኢትዮጵያ ዋነኛ አጋር መሆኗን ጠቅሰው፤የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ትሻለች ብለዋል።


የጀርመን ባለሃብቶች በአገሪቷ በተለያዩ የልማት ዘርፎች መዋዕለ ነዋያቸውን እያዋሉ መሆኑንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።


የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ለማቋቋም የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ ያጸደቀ ሲሆን፤በተያያዘም ምክር ቤቱ የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ 11 አባላት ያሉትን አገራዊ የምክክር ኮሚሽነሮች ምርጫ ማጽደቁ አይዘነጋም።


የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን መጋቢት 16 ቀን 2014 ዓ.ም በይፋ ሥራውን መጀመሩም ይታወቃል።

በተያዘው ክረምት የዝግጅት ምዕራፎች ተጠናቀው አገራዊ የምክክር መድረኮች በሕዳር ወር 2015 ዓ.ም የሚጀምሩ መሆኑን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በቅርቡ ለኢዜአ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።


ኢትዮጵያና ጀርመን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1905 ሲሆን ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ባላት የልማት ትብብር ማዕቀፍ በግብርና፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ በትምህርትና በሥርዓተ-ምግብ ድጋፎችን ታደርጋለች።


ኢትዮጵያና ጀርመን በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም የ100 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።


ድጋፉ ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል እንዲሁም የጀመረቻቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ ለውጦች ለማስቀጠል እንደሚውል በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም