ታዳጊዎቹ የት ነው ያሉት?

487

ታዳጊዎቹ የት ነው ያሉት?

  • ሰሞኑን ዶቸቨሌ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ አገኘሁት ባለው መረጃ በትግራይ ክልል ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ሲሆኑ ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ ግን ከአንድ ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ አይደሉም የሚል ዘገባ አውጥቷል።
  • ሮይተርስ በበኩሉ ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው ዘገባ አሸባሪው ቡድን ወጣቶችን አስገድዶ ለጦርነት እየመለመለ መሆኑን ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል በማለት አስነብቦ ነበር።
  • የዶቸቬሌን እና የሮይተርስን ዘገባ አገጣጥመን ስናየው በትምህርት ገበታቸው ላይ የሌሉት ታዳጊዎች የት ነው ያሉት? ብለን እንድንጠይቅ ግድ ይለናል።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ያቺ ጥቁር ቀን። ስለ ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ሲባል ባትፈጠር ይሻል ነበር። ዳሩ ምን ዋጋ አለው የእብሪተኞች ትዕቢት የፈነዳባት ቀን ሆነች። ከሀገር በተዘረፈ ሀብት ልቡ ያበጠበት ጁንታ በዚህች ቀን ያውም በውድቅት ሌሊት የሀገር ክህደት ሰይፉን መዘዘ። “ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል” እንዲሉ በአገር ክህደትና ዘረፋ የሰከረው አሸባሪው ህወሃት እብሪቱን መቆጣጠር ተስኖት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ክህደት በመፈፀም ኢትዮጵያን ‘አፈርሳለሁ’ የሚለውን ቅዠቱን የአደባባይ ሚስጢር አደረገው።

እናም ያቺ ቀን የአገር ዘብ የሆነው መከላከያ ሰራዊት የቆሰለበት፣ የደማበትና የአሸባሪውን ህወሃት የግፍ ጽዋ የተጎነጨበት ሆነ። መላው ኢትዮጵያውያንም የወጥቶ አደር ልጆቻቸው ዋጋ መክፈል ሀዘን ውስጥ ቢከታቸውም ባንዳውን የህወሃት ቡድን ይበልጥ ማንነቱን የተገነዘቡበትና ቡድኑን ለማክሸፍ ቆርጠው የተነሱበት ሆነ። አንድነታቸውን እንደ ብረት አጠንክረው እንደቀደምቶቻቸው የውስጥና የውጭ ጠላትን ለመመከት የሚነሱበት የማንቂያ ደወል፣ ለከሀዲያን እና ሴረኛ ባንዳዎች ደግሞ የውድቀታቸው መጀመሪያ ሆና አለፈች።

አሸባሪው ህወሓት ጥቅምት 24 አዳሩን በሰሜን ዕዝ ላይ ክህደቱን ፈፅሞ ማግስቱን ደግሞ አስቀድሞ ያዘጋጃቸውን አፈ ቀላጤ ሚዲያዎቹን በመጠቀም የትግራይን ህዝብ “ጦርነት ታውጆብሃል” የሚል ማወናበጃ ወሬ በመንዛት ሲመቸው “ትግራይን መቀበሪያ” እናደርጋታለን፤ ሳይመቸው ሲቀር ደግሞ “ተወረርን”  በማለት  ህዝብ እያደናገረ የጦርነት ቅስቀሳውን ቀጠለበት።

እነሆ አሁን አንድ ዓመት ከሰባት ወር በላይ አለፈ። በዚህ ከአንድ ዓመት በላይ በወሰደው ግጭት መንግስት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ቢያቀርብም ወትሮም ግጭትን የህልውናው መሰረት ያደረገው አሸባሪው ህወሓት የመንግስትን ጥሪ በመግፋት የትግራይን ህዝብ በተለይም አረጋውያን፣ ሴቶችና ህፃናትን ለከፍተኛ ችግር፤ ወጣትና ጎልማሶችን ለጥይት እራት በመዳረግ የትግራይን ህዝብ መከራ አበዛው።

ሰሞኑን ደግሞ ዶቸቨሌ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ አገኘሁት ባለው መረጃ ከአንድ ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ህፃናት በትምህርት ገበታቸው ላይ አይደሉም የሚል ዘገባ አውጥቷል። እንደ ዶቼሌ ዘገባ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ሲሆኑ ከዚያ በላይ የሆኑት ግን የሉም። በዚህ መረጃ መሰረት ከሰባተኛ ክፍል ጀምሮ ያሉ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ከሌሉ እነዚህ ታዳጊዎች የት ነው ያሉት? የሚል ጥያቄን ያጭራል። እነዚህ ታዳጊዎች ዕድሜያቸው በአማካይ ከ14 ዓመት በላይ ሊሆን እንደሚችል መገመት ለማንም አያዳግትም።

የሰሜን ዕዝን ጥቃት ተከትሎ በታወጀው “የህልውና እና የህግ ማስከበር ዘመቻ” በተካሄደው ጦርነት እጃቸውን ለመከላከያ ሰራዊት የሰጡ የአሸባሪዉ ቡድን ታጣቂዎች  አብዛኞቹ ታዳጊዎች መሆናቸውን ብዙዎች በአይናቸው ያዩት በጆሯቸው የሰሙት ሀቅ ነው።

ከሁለት ሳምንት በፊት ሮይተርስ ባወጣው ዘገባ ደግሞ አሸባሪው ቡድን ወጣቶችን አስገድዶ ለጦርነት እየመለመለ መሆኑን ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል በማለት አስነብቦ ነበር። እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ደግሞ ነዋሪዎች አንድም ልጆቻቸውን ለአሸባሪው እንዲዋጉ መስጠት አለባቸው አንድም ደግሞ በነፍስ ወከፍ ከአስር ሺህ ብር ያላነሰ ለቡድኑ ማዋጣት አለባቸው። ይህን ካላደረጉ ግን ለእስርና እንግልት ይዳረጋሉ።  ለጦርነት ከሚመለመሉት  ውስጥ ደግሞ ለታዳጊዎች እና ወጣቶች ላይ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ ዘገባው ያትታል።

የዶቸቬሌን እና የሮይተርስን ዘገባ አገጣጥመን ስናየው ከትምህርት ገበታቸው ላይ የሌሉት ታዳጊዎች አንድም የታጣቂ ማሰልጠኛ ካምፕ ናቸው ወይንም ደግሞ ግንባር ናቸው የሚል ትንታኔ የሚሰጥ አካል ቢኖር አይፈረድብትም። ካሁን በፊት ከጎንደር እስከ አፋር ካሳጊታ የተማረኩት ታጣቂዎች መረጃ የሚያሳየው ይህንኑ ነውና።

ገና ከጅምሩ ክልሉን እየመራሁት ነው የሚለው አካል “ጦርነቱን ህዝባዊ” አደርገነዋል፣ የጦር መሳሪያ ስለሌለን በህዝባዊ ማዕበል ነው ማሸነፍ የምንችለው  በሚል የተሳከረ ሃሳብ ለትግራይ ህዝብ ያለህን ይዘህ ውጣ የሚል መልዕክት በማስተላለፍ ነፍሰጡር እናቶች ሳይቀሩ በጦርነቱ መሳተፋቸውን ማንም አይዘነጋውም። ይህ አካሄድ ያሰጋቸው የክልሉ ተወላጆች ተተኪ ትውልድ ሊያሳጣ የሚችል ከባድ ችግር ይፈጥራል በሚል  በመገናኛ ብዙሃን ሲቃወሙ መቆየታቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

እጅግ የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ እዚህ የድሀውን ልጅ ከትምህርት ገበታው አፈናቅለው፤ ከእናቱ እቅፍ ፈልቅቀው ለእሳት ከፊት እያሰለፉ የራሳቸውን ልጆች ግን በአውሮፓና አሜሪካ ቅንጡ ዩኒቨርስቲዎች እያስተማሩ ሲያስመርቁ ትንሽ እንኳ የሀፍረት ስሜት የላቸውም። ድርጊቱ  ያስቆጣቸው በአዲስ አበባ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ትግራይ ልጆቿን በከንቱ መገበር የለባትም በሚል በአደባባይና በመገናኛ ብዙሃን ድርጊቱን ሲያወግዙትም ነበር።

አሁንም መንግስት በክልሉ የሰብአዊ ድጋፍ ያለገደብ እንዲደርስ በሚል የተናጠል የተኩስ አቁም ላይ ቢሆንም አሸባሪው ቡድን ግን አሁንም የጦርነት ነጋሪት መጎሰሙን አላቆመም። ታዳጊዎቹም ከትምሀርት ገበታቸው ላይ ተነስተው እንድም ተገደው አንድም ታላቋን ትግራይ እንገነባለን በሚል ቀቢፀ ተስፋ ተታለው በማሰልጠኛ ተቋማትና በጦር ግንባር መሆናቸውን የሚያመላክቱ መረጃዎች እየወጡ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ300 ሺህ በላይ ወጣቶች የት እንደገቡ ጠፍተውብኛል ሲል የክልሉ ወጣቶች ማህበር ከወራት በፊት መግለጫ አውጥቶ እንደነበርም አይዘነጋም። አሸባሪው ህወሓት እኔ ካልመራኋት ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ለሚለው ቅዠቱ የምስኪን ደሀ ልጆችን የጥይት ማብረጃ እያደረጋቸው ነው። ይሁን እንጂ ድርጊቱን የሚቃወሙ አካላት ወደፊት አለመግፋታቸዉና የዝምታው መስፈን ታዳጊዎች ዋጋ እንዲከፍሉ አድርጓቸዋል።

በተባበሩት መንግስታት የህፃናት መብት ኮንቬንሽን አንቀፅ 38 እንደተመለከተው ህፃናት ለጦርነት ያለመመልመል፣ ያለመሳተፍ እና የመሳሰሉት መብቶች አላቸው። ይሁን እንጂ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማትም ሆኑ ባለ ድርሻ አካላት ጉዳዩን ሲያወግዙት አይታይም። ስለዚህ ታዳጊዎቹ ከጦር መሳሪያ ይልቅ ደብተርና እስክርቢቶ እንዲይዙ ለማድረግ ቡድኑ ላይ ጫና ማሳደር ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም